የዩኒቨርሲቲዎች የታሪክ እይታ ከድጥ ወደ ማጡ
የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በአራት የዩኒቨርሲቲ መምህራን “የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ቀንድ ታሪክ፤The History of Ethiopia and the Horn” በሚል እርስ ለመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማስተማሪያ የሚሆን ጥራዝ አዘጋጅቷል። ዝግጅቱ ለመስከረም አልደርስ ብሎ ይሁን ሌላ ምክንያት ኖሮት ባይታወቅም ለሁለተኛው መንፈቀ ዓመት ሊሰጥ መታሰቡ ተሰምቷል። ስርጭት ላይ ሊውል የተቃረበ የሚመስለው ጥራዝ በሙያው ብቃት ባላቸው ምሁራን መዘጋጀቱም ተገልጧል፡፡ የታሪክ ትምህርት እንዳይሰጥ ተከልክሎ የቆየው የገዥው መደብ መጠቀሚያ ሆኖ ስለኖረ እንደ ገና በአዲስ መልክ መጻፍ አለበት ተብሎ መሆኑን ልብ ማለት ይገባል።
የታሪክ አጻጻፍ መርሕ የማይገዛ መሆኑ
ታሪክ የሚያጠና ሰው ሙያው መረጃን አሟጦ የመጠቀም ግዴታ ይጠበቅበታል። በተለይም ትውልድ የሚያንፅ መጽሐፍ አዘጋጅ ተብሎ የሚታጭ አካል የተጣለበትን ኃላፊነት የሚወጣ መሆኑ መረጋገጥ ይኖርበታል። ታሪክን ለማስተማሪያ ብሎ ለማዘጋጀት ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች ሙያዊ ዕውቀት ብቻ ሳይሆን ሥነ ምግባራቸው እና ሚዛናዊ አመለካከታቸው እምነት የሚጣልባቸው መሆን አለበት። ታሪክን ለማጻፍ የሚፈልገው አካልም ዕውቀትንና ችሎታን ወደ ጎን ብሎ በቀረቤታ፣ በወገንተኝነት፣ በቋንቋ መመሳሰል እየመረጠ የሚያጽፍ መሆን የለበትም። እንዲህ አይነት አሠራር የምንከተል ከሆነ ከማንወጣው አዘቅት ውስጥ እንደሚከተን በማሰብ ካለፈው ልንማር ይገባል። አሁንም ታሪክን ለፖለቲካ ትርፍ ለመጠቀም እና እውነት የሆነውን የሚገልጡትን ሳይሆን ለምናራምደው ፖለቲካ ይጠቅመናል ብለው ያሰቡትን ፈጠራ ማጻፍ ይጎዳናል። እዚህ ላይ ብላታ ደሬሳ አመንቴ ተናግረውታል ብሎ የልጅ ልጃቸው ሰለሞን ደሬሳ የጻፈውን መተግበር ታላቅነት መሆኑን ማስገንዘብ እንወዳለን።
ብላታ ደሬሳ አመንቴ የልጅ ኢያሱ ወዳጅ ነበሩ። ኢያሱ በራስ ተፈሪ ከሥልጣን ሲፈነገል ግን ከተፈሪ ጋር ተባበሩ። ምሥጢሩን የሚያውቁት ልጃቸው ይልማ ደሬሳ ለምን ወዳጅዎን ኢያሱን ትተው ከማይወዱት ተፈሪ ጋር ተባበሩ ሲሏቸው እሳቸውም እውነት ነው ለእኔ ኢያሱ ወዳጄ ስለሆነ ይጠቅመኝ ነበር። ለአገሬ ግን ተፈሪ ይሻላታል። እኔም የምተባበረው እኔን ብቻ ከሚጠቅመኝ ጋር ሳይሆን አገሬን ከሚጠቅማት ጋር ነው ብለዋል (ደቦ፣ 2010፣–)። ታላቅ የሚያሰኘውም እንደዚህ ዐይነት ተግባር መፈጸም ነው። ይህንን ስልት ፋሽስት ኢጣሊያ ልትጠቀምበት ፈልጋ ነበር። ጀግኖቹ እነ ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ ግን እኛ የተጣላነው ከተፈሪ እንጂ ከአገራችን ጋር አይደለም ብለው ተፋልመውታል። በዚህም ታሪክ በመልካም ሲዘክራቸው ይኖራል። ታሪካችንን ለመጻፍ የሚመረጡ አካላትም እንዲህ ያለ የመንፈስ ልዕልና ሊኖራቸው ይገባል። አድሎ እየሠሩ ሌላውን የመተቸት ሞራላዊ ልዕልና ሊኖራቸው እንደማይችልም ሊረዱት ይገባል።
የመሰለውን አፈ ታሪክ ጽፎ የምርምር ሥራ አስመስሎ ማቅረብ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደ ሚያመዝን ጸሐፊውም፣ አጻፊውም ሊረዱት ይገባል። የታሪክ ስሕተት ተፈጥሯል እያሉ የመጀመሪያም ሁለተኛ ደረጃም መረጃ የሚገኝላቸውን ትቶ አፈ ታሪክ ይዞ መቅረብ በምንም ተአምር በምርምር የተረጋገጠ የታሪካችን አካል ሊሆን አይችልም። የተወሰኑ አካላት ተመርጠው ቢጽፉት እንኳ ልዩ ልዩ ምሁራን ሊተቹበት ይገባ ነበር ብለን እናምናለን።
ታሪክን እንዲጽፉ የሚመረጡ ምሁራን የተማሩት ትምህርት ከሚጽፉት ርእሰ ጉዳይ ጋር ያለው ዝምድና መታየት አለበት። በሙያው ቢመረቁ እንኳ ከጣት ጣት ይበልጣል እንደሚባለው ያላቸው ልምድ፣ ተጠያቂነት፣ ተአማኒነት እና ሌሎችም ግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው ጉዳዮች መታየት አለባቸው። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ስንጠቀምበት የቆየው ስሕተት አለበት ሲሉ የቆዩት እነሱ ስላልጻፉት ነውም ያሰኛል።
ስንማረው የቆየውን የታሪካችን አካል አድርገን ለመቀበል ይቸግረናል ሲሉ የቆዩ እንደነበሩ ሁሉ ይህንንም የታሪካችን አካል አይደለም የሚሉ እንደሚነሡ ሊታወቅ ይገባል። ጸሐፊዎች ለአገር አሳቢነታቸው፣ ለትውልድ ተቆርቋሪነታቸው፣ የነገውን አገር ተረካቢ ኢትዮጵያዊ በጽኑ መሠረት ላይ ለመትከል ያላቸው ቀናዒነት መታየት ይኖርበታል። ከወገንተኝነት፣ ከአድሎ፣ የመንደር ወሬን የምርምር ውጤት አስመስሎ ከማቅረብ ነፃ መሆን ይገባቸዋል። እንዲህ ካልሆኑ ‹‹ታሪክ ለታመመ አእምሮ ፍቱን መድኃኒት ነው፤ History is a medicine for a sick mind›› (ሥርግው፣ 1972፣ መግቢያ) ብለው የሙያው ሊቃውንት የሚመሩበትን ዲስፕሊን መና ማስቀረት ነው።
ታሪክ ለመጻፍ የሚነሣ አካል ፖለቲከኞች ወይም የግል ጥቅም አሳዳጆች እናተርፍበታለን ብለው ካዘጋጁት የሐሰት ትርክት ነፃ መሆን ይኖርበታል። የተጻፉ እና የቃል አስረጅዎችን፣ አሉባልታ እና ስም ማጥፋቶችን አበጥረው እና አንጠርጥረው ወደ እውነት ለመጠጋት የሚያደረጉት ጥረት አስቀድመው ባበረከቷቸው ሥራዎቻቸው መገምገም ይኖርባቸዋል። የምንደኝነትን መሰናክል ዐልፈው የኖላዊነት እና የእውነተኛ መምህርነትን ተግባር የሚወጡ፣ ተማሪዎቻቸው ምናበ ሰፊ እንዲሆኑ እንጂ እገሌ ተነካብኝ ብለው አገር የሚበጠብጡ ምሁር መሳዮችን ለማውጣት የማይደራደሩ መሆን ይገባቸዋል።
በያዝነው የትምህርት ዘመን መንግሥት እስከ አሁን አገልግሎት ላይ የቆየውን የትምህርት ፍኖተ ካርታ መቀየሩን ገልጧል። ተቋርጦ የነበረውን የታሪክ ትምህርት እንደገና ለማስቀጠል የማስተማሪያ መጽሐፍም አዘጋጅቷል። እስከ አሁኑ ለየት የሚያደርገው አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ኢትዮጵያውያን የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት እና አሳብ አስተያየት የሰጡበት መሆኑ ነው። በዚህም ይበልጥ ኢትዮጵያውያንን የሚገልጽ አድርጎ ለማዘጋጀት መታሰቡን እንድንገምት አድርጎናል። መጻሕፍቱ ሲዘጋጁ የተነገረው በተግባር መገለጥ አለመገለጡን መጻሕፍቱ ተዘጋጅተው ሲቀርቡ የምናየው ይሆናል።
የጸሐፊዎቹ ማንነት
‹‹Module
for History of Ethiopia and the Horn For HLIS›› በሚል ርእስ የተዘጋጀውን ማስተማሪያ ጥራዝ ያዘጋጁት አካላት የትምህርት ሁኔታቸው ባይገለጥም ሦስቱ እስከ ሦስተኛ ድግሪ የተማሩ አንደኛው ደግሞ እስከ ማስተርስ የተማረ መሆኑ ተመልክቷል። ስማቸውም ሱራፌል ገልጌሎ (PhD) ከአዲስ አበባ ዩኒበርሲቲ፣ ደሬሳ ዴቡ (PhD) ከጂማ ዩኒቨርሲቲ፣ ደረጀ ሂነው (PhD) ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ እና መሠረት ወርቁ (MA) ከደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ናቸው። ሰዎቹን እንዴት እንደመረጣቸው የሚያውቀው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቢሆንም እነዚህ ሰዎች እስከ አሁን ሲዘጋጁ በነበሩ የታሪክ መጻሕፍት ላይ ተሳትፎ ስለማድረግ አለማድረጋቸው፣ ስለሚዛናዊ አስተሳሰባቸው የሚታወቅ ነገር የለም።
የምሁራኑን ማንነት ‹‹በ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ለዩኒቨርሲቲ እና ኮሌጆች የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች ከሚሰጡ ኮመን ኮርሶች (ሁሉን አቀፍ ትምህርቶች) አንዱ ለሆነው የታሪክ ትምህርት የተሰናዳው ማስተማሪያ መጽሐፍ ተከልሶ እና ተበርዞ መዘጋጀቱ ተጠቃሽ ነው። ሰነዱ ከ1990ዎቹ ወዲህ በተመረቁ አራት ወጣት መምህራን መሰናዳቱ ተሰምቷል። ሞጁሉ ከዩኒቨርሲቲዎች ቀድሞ እጁ የገባው (‹‹ሻዶው አዘጋጅ ሊሆንም ይችላል››) ጃዋር መሐመድ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ መለጠፉ ይታወሳል›› (ፍትሕ መጽሔት፣ ቍጥር 58 ታኅሣሥ 2012፣ 6) የሚለው ይገልጠዋል ብለን እናምናለን። ይህ ሐሳብ ብዙ ጉዳዮች እንደታጨቁበት መረዳት የሚገባ ሲሆን ብሉይን በአዲስ ለመተካት ያሰበ አካል አዲስ አቀራረብ እና የተለየ ነገር አቀርባለሁ ብሎ በማሰብ ሊያዘጋጀው እንጂ ሰው ስለተቀየረ ብቻ አዲስ ነገር እንደሚገኝ እያሰቡ ገንዘብን፣ ጊዜን፣ የሰው ኃይልን፣ ማባከን ተገቢ አለመሆኑን ማስገንዘብ እንወዳለን።
ከላይ ስማቸው የተጠቀሱት አካላት አዘጋጁት ተብሎ የቀረበው ማስተማሪያ ጥራዝ በዋናነት ቅኝት ላይ ያተኮረ፣ ከሀገር በቀል እና ግእዝ ምንጮች ይልቅ ለዐረብ የቃል ትውፊት ዕውቅና የሰጠ፣ ኢትዮጵያ እንደ ማኅበረሰብ ለሦስት ሺህ ዘመን የተጓዘችበትን መንገድ እና ዱካ አጥፍቶ ሌላ ለመገንባት የሞከረ ነው። አንዳንዶች እንደሚሉት ‹‹ሕወሐት በ1968 ዓ.ም ባወጣው የፓርቲው መግለጫ ትግሌ ጸረ ጽዮናዊ እና ጸረ አውሮፓ ኢምፔራሊዝም ነው ይልና ጓዳዊነቱን ወደ ዐረቡ ዓለም ያደላ መሆኑን ያትታል›› (የሺ ሀሳብ፣ 2012፣ 57-58) የተባለው በዚህ ጥራዝ ጎልቶ ወጥቷል። ይህ አስተሳሰብ አሁንም መስመር የያዘ እና ከአድሏዊ አመለካከት የጸዳ ባለመሆኑ በመጽሐፉ ተንጸባርቋል። የማስተማሪያ መጽሐፉ የሚፈልገውን ደግፎ የሚጠላውን ካጣጣለ በኋላ ማጣፊያው ስለሚያጥርበት ትምህርቱ ላይ ሳይሆን ስልቱ ላይ መጠበብ ያበዛል።
ያለፈውን ስሕተት የሚደግም መሆኑ
ታሪካችንን መማራችን የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም። የሚያከራክረው ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች በተግባር መገለጥ አለመገለጣቸውን ስንመረምር የምንደርስበት እውነት ነው። መጽሐፉ ግእዝንም፣ እንግሊዝኛንም ወደ ጎን ትቶ ዐረብኛ ምንጮች ላይ ብቻ ተንጠልጥሏል። ይህ የሚያመለክተው ደርግ የጀመረው ክርስትናን እና ምዕራባውያንን ገሸሽ አድርጎ ዐረቦችን የማቀፍ ስትራቴጂ እስከ አሁንም አለመስተካከሉን ነው። ከተጻፈ መረጃ ይልቅ አፈ ታሪክ ላይ መሠረት አድርጎ ሊያስደስታቸው የፈለጋቸውን አካላት ለማስደሰት ብዙ ታትሯል። ምን አልባትም አስቀድመን እንደጠቀስነው በክርስቲያኖች ላይ ጂሓድ ያወጀው አካል እንዲህ አድርጋችሁ ጻፉ ብሏቸውም ይሆናል። የሚበጀው ክርስቲያኑም፣ ሙስሊሙም፣ አባ ገዳውም፣ የባሕል እምነት ተከታዩም፣ ይሁዲውም ሆነ ፕሮቴስታንቱ ተችቶበት የተሻለ ሊያግባባ የሚችል ታሪክ ይዞ መቅረብ ነው። የዐረብ ምንጭ ለምን ተጠቀሙ ማለታችን ሳይሆን ለዚያ የተሰጠው ተአማኒነት ለሌሎች ለምን ተነፈገ ማለታችን ነው።
ለሃይማኖቶች የተሰጠ ሽፋን
መጽሐፉ ስለሃይማኖቶች ባቀረበው ሐተታ ውስጥ ባሕላዊ እምነቶችን በ3 ገጽ፣ ይሁዲነትን በ1 ገጽ፣ ኦርቶዶክስ ክርስትናን በ1 ገጽ፣ እስልምናን በ4 ገጽ ጠቅልሎ አቅርቦታል። አድሎው የሚጀምረው ከዚህ ነው። ከ34 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያን ስትሠራ ለኖረች፣ አገር ስትወረር አብራ ለመከራ እየተዳረገች ለመከራውም ለደስታውም ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ዕውቅና መንፈግ የጤንነት አይመስለንም። አልፎ አልፎ እንዲያውም ቂሙን ለመወጣት ሲሞክር ወይም ሌሎች የጫኑትን እውነት አስመስሎ ሲያቀርብ ይታያል።
ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የሚመጣ ሁሉ ማየት የሚፈልገው እና የሚመራመረው የቤተ ክርስቲያን አሻራ ባረፈበት ቅርሳችን መሆኑ እየታወቀ በረከቷን ፈልጎ እሷን መጥላት ምን አይነት ፈሊጥ ነው? ያሰኛል። በማያውቁት ወይም ቀርበው ባልጠየቁት በቤተ ክርስቲያን እና ሃይማኖታዊ ጉዳይ ገብቶ መዘባረቅም ከትችት አያድንም። የቤተ ክርስቲያን ሲሆን የማያውቁትን የገባቸው አስመስለው በማቅረብ እና ሾላ በድፍን አጠቃላይ ገለጣ ሰጥተው ያልፉና ስለእስልምና ሊያስረዱ ሲሞክሩ የሃይማኖት ሰባኪ ሆነው ያልተጻፈ የዐረብ ምንጭ ጠቅሰው እንድናምናቸው ይታትራሉ። ስለ ቤተ ክርስቲያን ሲጽፉ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ስም ለማጥፋት የተጠቀሙበትን እውነት አስመስለው ያቀርባሉ። ስለእስልምና ሲጥፉ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ታሪክ ጸሐፊዎች ያልደረሱበትን አፈ ታሪክ የዐረብ ምንጮች እንደሚገልጡ አድርገው ታሪክን ለማዛባት የሚችሉትን ያህል ጥረት ያደርጋሉ። እንዲህ አይነቱ ተግባር ትውልድን የሚያንጽ ታሪክ ይጽፋሉ ተብሎ ኃላፊነት ከተጣለባቸው ምሁራን የሚጠበቅ አይደለም።
ለሀገር ውስጥ መረጃ ምንጭ ትኩረት መንፈግ
ዜና መዋዕሎችን ከአፈ ታሪክ ጋር የተቀየጡ ብሎ የሚተቸው እና ገድላትን ከሃይማኖት ዐውድ ወጥተው ነገሥታት ሀገር ለማቅናት የሔዱበትን መንገድ እንደሚያሳዩ ብቻ አድርጎ የሚፈርጀው መጽሐፉ የአንድ የእስልምና እምነት ተከታይ ያልተጻፈ ታሪክ ጠቅሶ በትክክል የእስልምናን አስተምህሮ እንደሚያሳይ አድርጎ ያቀርባል። በአንፃሩ በገድላት ውስጥ የሚገኘውን ጽንዓት፣ሥነ ጽሑፍ፣ ሥነ ማኅበረሰብ፣ ባሕል፣ ፎክሎር፣ የጥንቷን ኢትዮጵያ አስተዳደር፣ ታሪክ፣ ወሰን አከላለል፣ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ የነበረውን ታሪካዊ ሁኔታ ለማጥናት እንደሚጠቅሙ ማሳየት አይፈልጉም። ስለእስልምና በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ተማራማሪዎች የተጻፉትን መረጃዎች ትቶ በቅርብ የተነሡ የተበድለናል ሮሮ የሚያሰሙ ወገኖች ደጋፊዎቻቸውን በስሜት ለመንዳት ያመቸናል ብለው የፈበረኩትን ልቦለድ እውነት አስመስሎ ያቅርባል። ይህም ጥላ ሆኖ መጽሐፉን ያጻፈ አካል አለ ተብሎ የተጠቆመው ወደ እውነት እንዲጠጋ ያደርጋል። ይህን ከመጽሐፉ በመጥቀስ እናብራራው።
መጽሐፉ በገጽ 15 እንዲህ ይላል “The value of Manuscript is essentially religious”፤ ‹‹የብራና መጻሕፍት ይዘት በዋናነት ሃይማኖታዊ ነው››የሚለው ጥቅል ፍረጃ የተሳሳተ ነው። ይህ ጥቅል ድምዳሜ ልምድ የሌላቸው አጥኝዎች የብራና መጻሕፍት ሃይማኖታዊ ናቸው በማለት እንዳይመራመሩባቸው መንገድም፣ ፍላጎትም ይዘጋል። ከብራና መጻሕፍት መካከል ዋና ትኩረታቸው ሃይማኖታዊ የሆኑም ያልሆኑም መኖራቸው በኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በውጭ ሀገር አጥኝዎች የተረጋገጠ ሆኖ ሳለ እዚህ ድምዳሜ ላይ መድረስ ተገቢ አይደለም። ለምሳሌ ጊዮርጊስ ወልደ አሚድ፣ መጽሐፈ ፈላስፋ ጠቢባን፣ መጽሐፈ መድኃኒት፣ አንጋረ ሰላስፋ፣ ፊሳሎጎስ፣ መጽሐፈ በርለዓም ወየወሴፍ ፣ የዓለም ታሪክ፣ ዐውደ ነገሥት፣ ልዩ ልዩ ዜና መዋዕሎች፣ ክብረ ነገሥት፣ ታሪከ ነገሥት እያሉ መጥቀስ ይቻላል። የጀርመን፣ የጣሊያን፣ የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ እና የእስራኤል የሥነ ገድል አጥኝዎች በብራና መጻሕፍታችን ሲመራመሩ የሚኖሩት ከሃይማኖታዊ ዐውድ የዘለለ ጠቀሜታ ስላላቸው መሆኑን ለጥራዙ አዘጋጆች ማስገንዘብ እንወዳለን። የውጭ አገር ተጓዦች የጻፏቸውን ማስታወሻዎች መጥቀሱ መልካም መሆኑን ብንጠቅስም ተማሪዎቹ ምርቱን ከገለባ ለመለየት እንዲችሉ አልፎ አልፎም ቢሆን ሒሳዊ ዳሰሳ ቢቀርብባቸው መልካም መሆኑን ለማስገንገብ እንፈልጋለን።
የተዘጋጀው ጥራዝ ስለክርስትና እንዲህ ይላል፡- “Evidences show that Aksumite king Ezana (r.320-360) dropped pre
christian gods like Ares (Hariman), Maharram(War gods), Arewe (serpant python
gods), Bahir(Sea gods) and Mider (earth gods) and embranced Christianity.
Instrumental in conversion were Syrian brothers, Aedesius and Fremnatos (page
38). አንድ ሀገር ምንም በክርስቶስ ያምናል ተብሎ ቢነገር ሙሉ በሙሉ ክርስቲያን ሆኖ ሕግጋቱን ጠንቅቆ ይፈጽማል ተብሎ አይታሰብም። አልፎ አልፎ ባዕድ አምልኮ እና በጣዖታት ማምለክ ሊኖር ይችላል። እንኳን በዚያን ዘመን ዛሬም ቢሆን ጣዖት ማምለክ አልጠፋም። ኢትዮጵያ በመንግሥት ደረጃ የጦርነት አምላክ፣ የባሕር አምላክ፣ የመሬት አምላክ እያለች ጣዖት አቆማ ታመልክ ነበር የተባለው ሊታመን የሚችል አይደለም። በግእዝ የተጻፈውን ቃል እንደ ባዕድ አምልኮ መቍጠር አለማወቅን ወይም ሌሎች ያሉትን ማስተጋባትን ያሳያል። አርዌ ማለት በግእዝ እባብ ማለት ነው። ባሕር ማለትም የውኃማ አካላት መጠሪያ ነው። ምድር ማለትም የደረቅ መሬት (የየብስ) መጠሪያ ነው። በድንጋይ ላይ ጽሑፎች እነዚህ ቃላት መገኘታቸው ኢትዮጵያ ባዕድ አምላክ ታመልክ ነበር ብሎ አፍን ሞልቶ ለመናገር ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም። የእነዚህ ፍጥረታት ሥዕል በሐውልቶች ላይ መገኘቱ በምን ምክንያት ከባዕድ አምልኮ ጋር እንደሚገናኝ የሚያውቁት በራሳቸው ሥነ ልቡና የእኛን ሀገር ታሪክ ለማጥናት የሞከሩ ነጮች እና አሁንም የእነሱን ሐሳብ ለመሞገት ሳይሆን እንዳለ ተቀብለው ለማስተጋባት የሚታትሩት የእኛው ወገኞች ናቸው። ለዚህም ቢሆን አሳማኝ መረጃ ማቅረብ ይኖርባቸዋል።
በሬ ወለደ ትርክት
ኢትዮጵያ በክርስትና ማመን የጀመረችው በ34 ዓ.ም በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በባኮስ ወይም በአቤላክ አማካኝነት ነው። የቍስጥንጥንያው ፓትርያርክ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ኢትዮጵያውያን በዕለተ ጰንጤ ቆስጤ በኢየሩሳሌም እንደተገኙ፣ ለሐዋርያት በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ያስተምሩ ዘንድ 71 ቋንቋዎች በተገለጠላቸው ጊዜ የበረከቱ ተሳታፊዎች እንደነበሩ ጽፏል። ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ ያላካተተበትንም ምክንያት በቍጥር ጥቂት ስለነበሩ መሆኑን አስረግጦ ተናግሯል። እሱ ብቻ ሳይሆን የላቲን ቤተ ክርስቲያን አባት የሚባለው አባ ጀሮም፣ ታሪክ ጸሐፊው ሩፊኖስ እና ሌሎችም ስለኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ሐዋርያዊ አገልግሎት ጽፈዋል። ጃንደረባው ለወገኖቹ ሐዋርያ ሆነ በማለት የመጀመሪያው የአፍሪካ ሐዋርያ መሆኑንም ተናግረዋል። ታሪክ ጸሐፊዎቻችን ማመን የማይፈልጉት ወይም እንደ አፈ ታሪክ የሚቈጥሩት ይህንን እውነት ነው። ይህን እውነት አልቀበልም ያለ ሰው የሌለ አፈ ታሪክ እየጠቀሰ እውነት ለማስመሰል ሞክሯል። ከተመራማሪ የሚጠበቀው ያልተሔደበትን መንገድ በምርምር ታማኝ ከሆነ መረጃ ላይ ደርሶ አዲስ እውነትን ማሳየት ነው።
ለምሳሌ ሥርግው ሐብለ ሥላሴ ስለዮዲት ጉዲት ጥንት ሲነገር ከነበረው የተለየ መረጃ ሲያገኙ ሁለቱንም አቅርበው ውሳኔውን ለአንባቢ ይሰጣሉ። የዚህ መጽሐፍ አዘጋጆች ግን ንጉሣችን አርማህን በቅርብ የተነሡ እና መረጃ የሌላቸው ወገኞች የሚያስተጋቡትን የሐሰት ትርክት እውነት አስመስለው ንጉሡን አስልመው ሲያቀርቡ ቤተክርስቲያን ምን እንደምትል ጠይቀው ማረጋገጥ አልፈለጉም። አንዳንድ የዐረብ ምንጮች ብለው ቢነግሩንም እስከ አሁን ያልተደረሰበት በዐረቦች እጅ የሚገኝ መረጃ እንደሌለ ሊታወቅ ይገባል። ኖሮ እኛ ብንደብቀው እንኳ ምዕራባውያን ከዐረቦች እኛ በልጠንባቸው እውነቱን ሸፍነውት እንደማይቀሩ ሊታወቅ ይገባል። ይህ ጉዳይ እውነት ቢሆን ኖሮ አሁን ተምረናል ብለው ከሚያስቸግሩ ወገኖች በተሻለ መልኩ ሊታመን እንዲችል አድርጎ የዘመኑን መንፈስ የጻፈው ዐረብ ፋቂህ ይመዘግበው ነበር። በእስልምና ላይ የተማራመሩት እነ ፕሮፌሰር ጆን ስፕንሰር ትሪሚንግ ሐም እና ሌሎችም መረጃ አግኝተው አያልፉትም ነበር። ይህን አምኖ ለመቀበል የቸገራቸው ታሪክ ጸሐፊዎች ያልተጻፈ ታሪክ ንጉሥ አርማህ ሰልሟል ብለው ሲጽፉ መረጃ ለመያዝ እንኳ አልፈለጉም።
እውነቱ ከቤተ መንግሥት ወገን የነበረው ኢትዮጵያዊው ባኮስ ክርስትናን ተቀብሎ ወደ አገሩ ተመልሶ ሲያስተምር መኖሩ ቢታወቅም በኋላ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንበረ ጵጵስናን ማምጣቱ ነው፡፡ የመንበረ ጵጵስና መገኘት ደግሞ በቀላሉ ካህናት እና ዲያቆናት እየሾሙ፣ በየቦታው አብያተ ክርስቲያን እንዲተከሉ ስለሚያደርግ ይህ የሆነው እ.ኤ.አ.330 ነው። የውጭ ሀገር ታሪክ ጸሐፊዎች የሚስቱት ወይም ሆን ብለው በዓላማ አድበስብሰው የሚያልፉት ይህን እውነት ነው። ኢትዮጵያ የግብፅ አንድ ሀገረ ስብከት ሆና ጳጳስ ሲሞትብን ግብፅ እየሔድን ስናመጣ መቆየታችን ዓለም ያውቀው ፀሐይ የሞቀው እውነት ነው። ኢትዮጵያውያን አስቀድሞ የጸና እምነት እንደ ነበራቸው የሚያስገነዝበው ነገሮችን ሁሉ በእምነት ዓይን ብቻ የተመለከተው የቅዱስ አትናቴዎስ ንግግር ነው። ካለ ሰባኪ በማመናችን ተደንቆ ለጵጵስና የምትገባው ቋንቋቸውን የምታውቀው አንተ ነህ ብሎ ጳጳስ አድርጎ ላከልን። ዛሬ ቢሆን ኖሮ ከሶርያ መጥተህ እንለው ነበር። ከሰሜን መጥተህ፣ ደቡብ መጥተህ፣ እዚህ ማገልገል ካለብሔርህ አባታዊ መልእክት ማስተላለፍ አትችልም እንለው ነበር። እውነት የሆነው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ባኮስ አስቀድሞ በቤተ መንግሥት ሲያስተምር የኖረውን እና ተተክሎ እንዲቆይ ያደረገውን የክርስትና ትውፊት አባ ሰላማ በክህነት ማጽናቱ ነው።
ምንም እንኳ ክርስትና አስቀድሞ በባኮስ ቢሰበክ አባ ሰላማ ሙሉ አደረገው። የጎደለውን ሞላው፣ ሊላላ የነበረውን አጠበቀው። ክርስትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሃይማኖት እንዲሆን አባ ሰላማ የበኩሉን አስተዋጽዖ አደረገ። ምዕራባውያን የሚሸሹት ይህንን እውነት ነው። ይህንን እውነት የማይቀበሉትም ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ቀድማ ክርስትናን ተቀበለች ብለው ማመንም፣ መስማትም ስለማይፈልጉ ነው። ታሪካችንን ወስደው እና የመካነ ሥላሴ መነኩሴ ከሆነው ከአባ ጎርጎርዮስ ታሪካችንን ተምሮ ስለኢትዮጵያ የጻፈውን ኢዮብ ሉዶልፍ የአፍሪካ የታሪክ አባት ሲሉት ስለመምህሩ አባ ጎርጎርዮስ ማንሣት አይፈልጉም። መታወቅ ያለበት ክርስትናም፣ እስልምናም በኢትዮጵያ ላይ የራሳቸውን አሻራ ማሳረፋቸው ነው። ፖለቲካ በተቀያየረ ቍጥር መንግሥትን እየተጠጉ የክርስትናን አሻራ ለማጥፋት መሞከር ዕልቂትን እንጂ ሰላምን አያመጣም። የሚገባው የሁሉንም ወገኖች ታሪክ ሚዛናዊ አድርጎ ማቅረብ እና ሁለቱም ታሪካችን የኢትዮጵያዊነት መታወቂያችን መሆኑን አምነን መንከባከብ ነው። የእኛን እያፈረሱ የእነሱን እንድንቀበል መሞከር ግን ታሪክን በታሪክ ሊቃውንት ስም ሸፍኖ ከመካነ አእምሮዎቻችን ውስጥ ማስገባት በመሆኑ ሊያስማማን አይችልም። እውነት ከሆነም በግልጽ ይቅረብና ተካራክረን እውነት አርነት ያወጣው የታሪካችን አካል ሆኖ ይቀጥል።
ነጮች በዓላማ ያበላሹትን የታሪክ ጥናት እንደ እውነት በመያዝ የጥፋት ዓላማ አስፈጻሚ ከመሆን ይልቅ በሚገባ ተመራምሮ እውነት ከሆነው ዘንድ መድረስ ይገባል። የተለመደው የተሻለ ነገር ሳይዙ ከባለ ጊዜ እየተጠጉ ታሪክን መሸርሸር ነው። ይህ መቆም ይኖርበታል። እንዳይቆም ብንፈልግም ዘመኑ በየስርቻው የተደበቀውን እውነት እየመዘዙ ሐሰተኛን የሚረቱበት በመሆኑ ታሪክ ጸሐፊዎቻችን ወደ ተሻለ እውነት የሚያደርሰንን መረጃ አቅርቡልን እንጂ ተጨማሪ ብጥብጥ አትፍጠሩ። የነጭ እና የዐረብ የጥፋት ዓላማ አስፈጻሚዎች አትሁኑ። የጣሊያን እና የዐረብ ዓላማ አስፈጻሚዎች ክርስትናን የተቀበልንበትን ዘመን ለሦስት መቶ ዓመታት ወደ ኋላ ይገፉታል። ይህንን የሚያደርጉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አሻራ ለማደብዘዝ ነው። ለእነርሱ የሚቀለውም ወገኖቻችንን በማስተማር ስም ዓላማቸውን ጭነው በመላክ ጠበቃ እንዲሆኗቸው ማድረግ ነው።
ዶግማን ማዛባት
በመጽሐፉ ገጽ 39 “In 16th and 17th centuries, Jesuits tried to convert Monophysite
EOC to Dyophysite catholic” የሚለው መረቅ እና ፍትፍት የተቀላቀለበት ነው። ካቶሊኮች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮችን ካቶሊካዊ ለማድረግ፣ ክህነትንም ከግብፅ ከሚመጣ ጳጳስ ከሚሰጥ ይልቅ ከሮም በሚላክ ጳጳስ እንደገና እንድንቀበል ሞክረው ነበር። በዚህም ምክንያት ብዙ ደም መፍሰሱ እውነት ነው። ትክክል ያልሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን እምነት ጠላቶቿ ስም ለማጥፋት የሚጠቀሙበትን ቤተ ክርስቲያናችን እንደምታምንበት አድርጎ “Monophysite” ብሎ መጥራቱ ነው። ይህ ቃል የግሪክ ሲሆን ትርጉሙም መለኮት ሥጋን ዋጠው፣ መጠጠው እና ባሕርይውን በማጥፋት አንድ ባሕርይ ሆነ ማለት ነው። ይህ ደግሞ ከቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ያፈነገጠ ነው። የሚቀጠለውም ለአውጣኬ ኑፋቄ ነው። የቤተ ክርስቲያናችንን አስተምህሮ በትክክል የሚገልጠው “Miaphysite” የሚለው የግሪክ ቃል ነው። ትርጉሙም ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ፣ ከሁለት አካል አንድ አካል በተዋሕዶ ከበረ ማለት ነው። ተዋሕዶውም በመጠፋፋት ሳይሆን በተዓቅቦ ሥጋም ባሕርይውን ሳይተው፣ መለኮትም ባሕርይውን ሳይለቅ የተፈጸመ መሆኑን አምኖ መመስከር ነው። ዋጠው መጠጠው በጉባኤ ኬልቄዶን የተሰበሰቡ መለካውያን አውጣኬን የከሰሱበት ኑፋቄ ነው። መለካውያን የኦርቶዶክስን አስተምህሮ ወደ አውጣኬ ለማስጠጋት የሚጠቀሙበት ስም ቤተ ክርስቲያንን አይወክልም። ቅዱሱ አባት ዲዮስቆሮስ ምንታዌን አልቀበልም ስላላቸው ድሮም አለቃቸው ሊዮን በሚገባ ሳይረዳው የኖረውን ቃል በክህደት ስላጸናው እምነታችንን “Monophysite” ብለው መጥራት ጀመሩ። ስሕተት የሚሆነውም ሰዎች ያላሉትን የሚያምኑበት አስመስሎ እንዲህ ነው የሚያምኑ ብሎ መናገር እና ሌሎችንም ለማሳመን መሞከር ነው። ስለዚህ ካቶሊካውያን ሊቀይሩ የመጡት ሃይማኖታችን Monophysite ሆኖ ወደ Dyphysite ሳይሆን “Miaphysite” ብለን የምናምነውን
Dyphysite ብላችሁ እመኑ ብለው ነበር። ስላልተሳካላቸውም የብዙ ኢትዮጵያውያን ደም ፈሰሰ።
የቤተ ክርስቲያንን ውለታ ጥላሸት መቀባት
“EOC
Spread to centeral, south, east and west parts following their conquest by the
northern Christian kingdom. People were baptized as a government obligatory
decree. Lately monopolization of burial places by church forced people to
accept Tewahdo (page 39). ይህንን አንቀጽ የጻፈው ደጋፊ ለማግኘት የሚሻ ፖለቲከኛ ቢሆን ባልገረመንም ነበር። የጻፉት ግን በታሪክ ምሁራን ስም የተሰበሰቡ እና መንግሥት ትውልድ ይቀርፃሉ ብሎ ኃላፊነት የጣለባቸው ምሁራን ናቸው። እነዚህ ምሁራን ሲባል የሰሙትን በምርምር ማረጋገጥ ሲገባቸው ለኢትዮጵያ አንድነት የማዕዘን ድንጋይ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያንን መምታት ዓላማችንን ያሳካልናል ብለው ያሰቡ ወገኖች ላለፉት አምሳ ዓመታት በሐሰት የፈበረኩትን ፕሮፓጋንዳ እውነት አስመስለው የታሪክ ሰነድ አድርገው አቀረቡልን። ሰነዱ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ፣ እንደ ፈጠራ ሥራ አንድ ቦታ ቁጭ ብለው የጻፉት እንጂ በምርምር ያረጋገጡት አለመሆኑን ከሚያስገነዝበው ጉዳይ አንዱ ቤተ ክርስቲያን የመንግሥትን እጅ ጠምዝዛ የፈለገችውን ስታስፈጽመው የኖረች አስመስሎ ማቅረቡ ነው። በሌላ አነጋገር መንግሥት አገር መምራቱን ትቶ ቤተ ክርስቲያንን ከጎኑ አድርጎ ወንጌል ሲሰብክ የኖረ ያስመስላል። ይህ ሐሳብ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥቃት እና እንዳትናገር ለማሸማቀቅ ያስችለናል ብለው የፈጠሩት ነው። በዘውዳዊው አገዛዝ የተማረረውና መፍትሔውም እግዚአብሔርን መካድ የመሰለው ማርክሲዝምን ርዕዮተ ዓለም አድርጎ የተነሣው የሶሻሊስት አቀንቃኝና የብሔር ፖለቲካን ቀይጦ የያዘው ወጣት በአንድነት ተስማምቶ የገዛህ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንም ጭምር ናት ብንለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሰማናል ብለው ከመምህራቸው ከሌሊን የተማሩትን ሊያስተምሩን ነው። ማንም ምሁር በእውነት ላይ ተመሥርቶ ይህንን ትርክትና ርዕዮት ሊቃወም ከተነሣም በሳይንሳዊ መንገድ እና በምርምር ሳይሆን የድሮ ሥርዓት ናፋቂ በማለት እናሸማቅቀዋለን ብለው የፈጠሩት መሆኑን መረዳት ይገባል። ይህን ሐሳብ ላለፉት አምሳ ዓመታት ሲያስተጋቡት እንደኖሩ አሁንም ምሁር በሚሏቸው ሆድ አደሮች ይህንኑ ሐሳብ በከፈቷቸው ብዙኃን መገናኛዎች ሲያደነቁሩን ውለው እንደሚያድሩ ይታወቃል።
በፖለቲካ ፍልስፍና ግራ የተጋቡና የራሳቸው ሀገር በቀል መፍትሔ ማመንጨት የተሳናቸው የሐሳብ መካን የሆኑ ምሁራን ትውልድ የሚጠቅም አጀንዳ ስለሌላቸው ‹የሞኝ ልቅሶ መልሶ መልሶ› እንዲሉ ይህንን ያህል ዘመን ተናግረው አልሰለቻቸውም። የሚያመዛዝን አእምሮ ያለው ሰው አልቀበላቸው ስላለ ዩኒቨርሲቲዎቻችንን ጥላ አድርገው ቀረቡ። ለሀገር ሰላምና ለሕዝብ አንድነት የማይጠቅምና ግጭትን በትምህርት ስም በዘለቄታዊነት ለመትከል የሚሠሩ የሀገርና የእውነት ጠላት ብቻ ሳይሆን የቤተክርስቲያን ፀር የሆነ አቋም ይዞ የወጣቱን ትውልድ አእምሮ በሐሰት ለማጠብ መመኮር፣ ክርስቲያኖችን ብቻ ሳይሆን ለእውነት የመቆሙትን ሁሉ የሚያስቆጣ ተግባር ነው፡፡
ሀገር የሚያንጽ ተግባር ከመፈጸም ይልቅ ቡድናዊነት የሚበልጥባቸው፣ ትውልድ ሲበጠበጥ የትርፍ እንጀራችንን እንጋግራለን ብለው ያሰቡ ወገኖች የፖለቲካ መርሐ ግብር አድርገውት የኖረውን ሰነድ ለታሪክ ማስተማሪያ አድርገው አቀረቡልን። ከ1966 ዓ.ም በኋላ ሥልጣን ላይ የወጡ አካላት አፍቃሬ ዐረብ በመሆናቸው ቤተ ክርስቲያንን በመጥላት ያልተጻፈ ስምምነት ነበራቸው። ‹‹የኅብረተሰባዊነት አብዮት ከኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና ይልቅ ለእስልምና የተሻለ ዕድል ነበረው።…በኢትዮጵያም በ1968 ዓ.ም የሞስሊሞች ምክር ቤት (ሙጅሊስ) ተቋቁሟል›› (የሺህ ሀሳብ፣ 2012፣ 144-145) የሚለው ከትናንት እስከ ዛሬ ባለመስተካከሉ ለማስተካከል ጥረት ማድረግ ከኦርቶዶክሳውያን ሁሉ ይጠበቃል። ቤተ ክርስቲያን ያበረከተችውን እየተጠቀሙ ቤተ ክርስቲያንን ሲያሳድዱ መኖራቸው የሚያስቅም፣የሚገርምም ነው። የፊውዳሉ ሥርዓት ጠበቃ አድርገው በጭፍን ስለሚጠሏት በተባራሪ የሰሙትን ሁሉ እውነት አስመስለው ያቀርባሉ።
በመጀመሪያ ደረጃ ቤተ ክርስቲያን መንግሥትን እየተከተለች፣ በጦር እያስፈራራች ሃይማኖቷን እንዳስፋፋች አድርጎ ማቅረብ የተዛባ አስተሳሰብ የወለደው መሆኑን መናገር እንፈልጋለን። ይህ ብቻ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያኗን ታሪክ በማዛባት የቀረበው ሐሳብ እንዲስተካከል እንጠይቃለን።
እውነቱ ግን በተቃራኒው ነው። ቤተ ክርስቲያን ያለሰለሰችው የአረማውያን እና የአሕዛብ ልቡና ወደ ማእከላዊ መንግሥት ለመታቀፍ እንዳላስቸገረ እና መንግሥት የራሱን ሥራ ለመሥራት እንዳገዘው መረዳት ይገባል። ያለፈው ሥርዓት ፈጽሞታል ለሚሉት ጥፋት ቤተ ክርስቲያንን ተጠያቂ ማድረግ አንደበቷን ዘግታ እንድትቀመጥ ለማድረግ የተሸረበ ሴራ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ገለጻው እውነታን ያላገናዘበ መሆኑን መረዳት እና ተገቢውን መልስ መስጠት አስፈላጊ ሲሆን በሕግ መጠየቅ ይገባል። የኢትዮጵያ ሠራዊት ምን ያህል የተደራጀ ሆኖ ሀገር እንደ ወረረ የሚያውቁት ጸሐፊዎቹ ናቸው። ራሱን ቅኝ ተገዥ አድርጎ የሚያይ ምሁር ግራ ቀኝ አመዛዝኖ ታሪክን ይጽፋል ተብሎ አይታሰብም።
ንጉሡን አጅቦ የሚሔድ ሠራዊት መኖሩ ባይካድም አገር ስትወረር ኢትዮጵያዊው ገበሬ ቤት ንብረቱን ትቶ እየዘመተ ሀገር ሲጠብቅ የኖረ እንጂ ለቤተ ክርስቲያን ቀኝ እጅ ሆኖ ያላመኑት በግዳጅ እንዲጠመቁ ሲያደርግ አልኖረም። ወታደር ሆኖ ሀገር የጠበቀው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ የሆነው ብቻ ስለሚያስመስል ሌሎች እየኖሩ ያሉት ኦርቶዶክሳውያን በጠበቋት ሀገር ነው እንዲባል ራሳቸውን እንዳጋለጡ ጸሐፊዎች አልተረሰዱትም። እንዲህ አይነት መረጃ ካለም አምጥቶ መከራከር ነው። ሀገር ሲጠብቅ የኖረው ወታደር እንኳን ለሌላ የሚተርፈው ለራሱ የሚሆነው የሃይማኖት ትምህርት አልነበረውም።
በደቡብም ሆነ በምሥራቅ እና በምዕራብ ኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት የተተከሉት ከቤተ ክህነት በተሰጠ ተልእኮ ሳይሆን በሊቃውንቱ እና በካህናቱ ግለሰባዊ ጥንካሬ አማካኝነት ነው። ካህናት፣ መነኮሳት እና ሊቃውንት ከሰሜን ወደ ደቡብ ተዘዋውረው ያረፉበትን አካባቢ ነዋሪ አስተምረው አንዳንዶችም ቤት ንብረት አፍርተው መኖራቸው አይካድም። ይህ ደግሞ ሀገራችን ብለው የፈጸሙት፣ ከእግዚአብሔር እናገኘዋለን ብለው ያከናወኑት እንጂ ለመንግሥት ቀኝ እጅ ለመሆን አይደለም።
የቤተክርስቲያን መዋቅር ከነገሥታት ጋር እጅ እና ጓንት ሆኖ መንግሥት ወግቶ ድል ሲያደርግ ቤተክርስቲያን አስገድዳ ታጠምቅ ነበር የሚለው ፈጠራ እንጂ በመረጃ የሚረጋገጥ እውነት አይደለም። ይህ በማን ዘመነ መንግሥት እና መቼ፣ በየትኛው የኢትዮጵያ ክፍል እንደተፈጸመ ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል። ቤተክርስቲያን በማስገደድ ርስት ነቅላ፣ ሃይማኖት አስቀይራ አታውቅም። ‹‹የእምየን ወደ አብየ›› ከሆነ አንገት በመቅላት እስከ ዘመናችን የደረሰው፣ አሁንም በጥንቱ እኩይ ድርጊቱ የቀጠለው ማን እንደሆነ ይታወቃል። ታሪክ ጸሐፊ ተብለው የተሰየሙት አካላት ይህንን እውነት እንዳይናገሩ ወይ ፈርተዋል አልያም በገንዘብ አፋቸውን ተለጉመዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያንን የመንግሥት ቀኝ እጅ አድርጎ ማቅረብ
ከጥንት እስከ ዛሬ ቤተክርስቲያን የተስፋፋችው በገዳማውያን እንጂ በመንግሥት ደጋፊነት አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ መንግሥት ሲሳሳት በመገሠጻቸው ለመከራ የተዳረጉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መነኮሳት እንጂ የሌላ እምነት ተከታዮች አይደሉም። በመነኮሳቱ ድርጊት የተበሳጩት ዓፄ ዐምደ ጽዮንም፣ ልጁ ሰይፈ አርዕድ፣ ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ አቡነ ተክለ ሐዋርያትን ያሰቃዩዋቸው እና ከገዳማቸው አስወጥተው ያሳደዷቸው ክርስቲያኖችን እንጂ ሌሎችን አይደለም። ይህ ደግሞ የመንግሥት ቀኝ እጅ መሆናቸውን ሳይሆን እንዲያውም ባጎረስኩኝ እጄን ተነከስኩኝ ይፈጸምባቸው እንደነበር ነው። ቤተ ክርስቲያን ለመንግሥት ቀኝ እጅ ከሆነች መንግሥታት ለምን መነኮሳቱን ሲያሰቃዩ ኖሩ ብሎ መጠየቅ ከስሕተት ያድናል (ገድለ ፊልጶስ ዘደብረ ሊባኖስ፤ ገድለ አኖሬዎስ፤ ገድለ አሮን መንክራዊ፤ ገድለ አቡነ ተክለ ሐዋርያት፣ ተክለ ጻድቅ፣ 1966፣ 49-53) መመልከት ይቻላል።
አቡነ ኢየሱስ ሞዓ መጻሕፍትን ሲጽፉ ከኖሩበት ደብረዳሞ ገዳም ወደ ሐይቅ ሲመጡ በጣም ብዙ የብራና መጻሕፍትን ይዘው መጥተው የትምህርትም የምንኩስናም ማእከላቸውን ሐይቅ ላይ አድርገው ያስተማሯቸው ደቀ መዝሙሮቻቸው አቡነ ኂሩተ አምላክ ወደ ምዕራብ በመሔድ እስከ ቋራ አስተምረው ጣና ገዳማት ላይ ዐረፉ፤ አቡነ እንድርያስ ከኤርትራ ጀምረው እያስተማሩ እስከ ደቡብ ጎንደር መጡ፤ አቡነ ዜና ማርቆስ ዐባይን ተሻግረው ጎጃም አቸፈር ጣዖት አምላኪ የነበረውን ገዢ አሳምነው ከዚያ ቤተሰብ አባ ዓምደ ሥላሴን አፍርተው ማኅበረ ሥላሴ ገዳም እንዲመሠርቱ አድርገው እስከ ሱዳን አስተማሩ። አባ በኪሞስ ወይም ተከሥተ ብርሃን ዲማን እና አካባቢውን እስከ ይልማና ዴንሳ፣ ዑራ ኢየሱስ እና ናዳ ማርያም ድረስ አገውን ጭምር አስተማሩ። አባ ተጠመቀ መድኅን ከምዕራብ ሸዋ ተነሥተው ሙሉ መተከልን፣ አቡነ ዜና ማርቆስ በምድረ ጉራጌ እስከ ምሁር ኢየሱስ፣ አቡነ አኖሬዎስ እስከ ባሌ፣ አቡነ ሳሙኤል እስከ ደብረ ወገግ እና የአሁኗ ጂቡቲ ሲያስተምሩ የትኛው ወታደር አጅቧቸው እንዳጠቁ እና አስገድደው የነባሩን ነዋሪ ርስት እንደወረሱ የሚያውቁት የሐሰት ትርክት ጽፈው እውነት የሚያስመስሉ የዚህ የታሪክ ጥራዝ ጸሓፊዎች ናቸው፡፡
በተደጋጋሚ እስከ ወግዳ እየተስፋፋ እና እስከ ጀማ ወንዝ ድረስ እየሔደ የሸዋ ገዥዎችን እና ማእከላዊውን መንግሥት ያስቸግር የነበረውን ሞቶሎሚን ከድርጊቱ እንዲታቀብ እና በጦርነት ኪሳራ እንጂ ትርፍ እንደሌለ እንዲረዳ ያደረጉት አቡነ ተክለሃይማኖት አጥምቀው ፍሰሐ ጽየን ካሉት በኋላ ነው፡፡ ከዚያ በመቀጠልም አቡነ ተክለ ሃይማኖት እስከ ነጭ ዐባይ ድረስ ዞረው ሲስተምሩ ወታደር ይቅርና ረድዕ እንኳ አብሯቸው አልነበረም። እነዚህን እና ሌሎችንም አባቶች የየትኛው ንጉሥ ሠራዊት እንዳጀባቸው፣ ማን በሚባለው ጳጳሳችን የቤተ ክህነትን ተልእኮ እንደሰጣቸው አልነገሩንም። አሁን ታሪክ ተብሎ የቀረበልንን ዓፄ ምኒልክን ለማጣጣል እና ኢትዮጵውያንን በማሸማቀቅ የፈለግነውን ለማድረግ ይጠቅመናል ብለው አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ሲቀሰቅሱበት የነበረ የፖለቲካ መርሐ ግብራቸው ነው። ይህን አፈ ታሪክ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቀበለናል ብለው ማቅረባቸው ያስገርማል። እውነት ቢሆን እንኳ በመረጃ አስደግፈው ማቅረብ ነበረባቸው።
ለጥንቱ ሠራዊት ያለ ስሙ ስም መስጠት
በታሪክ ሰነድ እኛ ብቻ ሳንሆን የውጭ አገር ተጓዦች ጭምር ጽፈውት የምናነበው የዓፄ ምኒሊክ ሠራዊት በራስ ወልደ ጊዮርጊስ እየተመራ እስከ ሩዶልፍ ሐይቅ ድረስ እንደዘመተ ተዘግቧል። ከሠራዊቱ ጋር አብሮ የዘመተው ሩሲያዊ በዓይኑ ያየውን፣ በጆሮው የሰማውን በሦስት መጻሕፍት አስነብቦናል። ከዓፄ ምኒልክ ሠራዊት ጋር፣ ከእንጦጦ እስከ ባሮ እና በቅርብ ወደ አማርኛ በተተረጎመው የዓፄ ምኒልክ ሠራዊት ታሪክ የተረከበት መጻሕፍት የሠራዊቱን ድካም ቢነግሩንም ማንንም አረማዊም ሆነ የሌላ እምነት ተከታይ አስገድደው ክርስቲያን እንዲሆኑ ማድረጋቸውን አልመዘገቡም። በመዋቅር ደረጃ ተልእኮ የተሰጠው አንድም ቄስ አብሮ መጓዙን መጻሕፍቱ አይነግሩንም፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊት በምርኮ ድል ያደረገውን ሕዝብ በግዳጅ ለማጥመቅ የቤተክርስቲያን ቀኝ እጅ ሆነ ተብሎ መልካም ባደረገ እና ሀገር ጠብቆ ባቆየ መተቸት አልነበረበትም። ወታደር በሔደበት እንደሚወር፣ ተገዳዳሪውን እንደሚያውክ ቢታወቅም የራሳችንን ሀገር ሠራዊት ያለ ስሙ ስም መስጠት ተገቢ አይደለም ብለን እናምናለን።
ራስ ወልደ ጊዮርጊስ እስከ ሩዶልፍ ሐይቅ ሲዘምቱ እና የተበታተነውን መልሰው ሲሰበስቡ ታቦታ ይዘው አልዘመቱም። ነገሥታት ታቦት ይዘው የሚዘምቱት የውጭ ወራሪ ሲመጣባቸው እንጂ በሀገር ውስጥ አመጸኛ ሲነሣባቸው አለመሆኑን የታሪክ ድርሳናትን ማበላበጥ ከስሕተት ያድናል። ነገሥታት በሰላም ጊዜ የሚቀደስበት፣ በመከራ ጊዜ ካህናት ሱባኤ ይዘው መከራው እንዲርቅ የሚያደርጉበትን ታቦት ይዘው ቢዘምቱ ነውሩ ምኑ ላይ ነው? ነውር የሚሆነው ቤተ ክርስቲያን እና ምእመናን ሲፈጽሙት ነው እንዴ? ቤተ ክርስቲያን ከሠራዊታችን በየተዘዋወረበት አብራ እንደ ዘመተች ተደርጎ መጻፉ ሐሰት ነው፡፡ ራስ ወልደ ጊዮርጊስ የአካባቢውን ሰላም ካረጋገጡ በኋላ የከፋ ገዥ ተደርገው ሲሾሙ የሚስቀድሱበት ቤተ ክርስቲያን ማሠራታቸው፣ በቤተ ክህነት ደረጃ ባይሆንም በግላቸው ቄስ ወስደው ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ ማድረጋቸው እውነት ነው። ኦርቶዶክስ በሰላማዊ መንገድ የሠራችው እንደ ጥፋት ከተቈጠረ ከጀርመን መጥቶ በምዕራብ ወለጋ፣ በከፋ፣ በሲዳሞ፣ በጋሞ ጎፋ የፈጸመው ምን ሊባል ነው፡፡ እንደ Johann Ludwig Krapf ያሉ ጀርመናውያን ከ1837 እ.ኤ.አ. የኦሮሞን ሕዝብ ከግእዝ እና ከኢትዮጵያዊነት ለመነጠል የፈጸሟቸውን ጥፋቶች ተከትሎ በተከታታይ እስከ ዛሬ ምን እየተሠራ እንደሆነ ታሪክ ጸሐፊዎች ለመግለጥ አለመፈለጋቸው እውነትም ከታሪክ ጸሐፊነት ይልቅ አንድ የተደበቀ ርዕዮተ ዓለም የሚያራምዱ መሆናቸውን ይገልጣል፡፡ ከዐረብ የመጣው እስልምና ኢትዮጵያውንን ባርያ ብሎ እየፈነገለ ለዐረቦች ሲቸበችብ መኖሩን እነ አባ ጅፋር ሲፈጽሙት የኖሩትን የታሪክ መጻሕፍትን ማየት በቂ ማስረጃ ያስገኛል፡፡
ራስ ዳርጌ አርሲን ሲያስገብሩም ቤተ ክህነት አብራ አልዘመተችም። ምኒሊክ ሐረርን አስገብረው ከመሐል ሀገር ጋር ሲያስተሳስሩም ቤተ ክህነት አብራ አልነበረችም፡፡ ነበረች የሚል አካል ካለ መረጃውን ያቅርብ። የሆነው የሚያምኗቸውን የሐረርጌ ገዥ ለማድረግ ፈቃደኝነታቸውን ሲጠይቋቸው በማናውቀው ባሕል መካከል አንኖርም በማለታቸው ደጃዝማች መኮንን ወልደ ሚካኤልን ገዥ አደረጓቸው፡፡ ደጃዝማች መኮንንም በሐረርና አካባቢው ቤተ ክርስቲያን ያስፋፉት የአካባቢውን ሰው አሰገድደው ሃይማኖቱን በማስቀየር ሳይሆን ከሌላ አካባቢ ካህናትን በማምጣት ነው፡፡ አብሮ በመኖር አንዳንድ ክርስቲያኖች እስልምናን መቀበላቸው፣ አንዳንድ ሙስሊሞችም ክርስትናን መቀበላቸው ሊከሠት ይችላል። ጊዜ ያገኘ ሲመስለው ክርስቲያኑ ሙስሊሙን፣ ሙስሊሙም ክርስቲያኑን አሰቃይቶ ሊሆን ይችላል። አንድ ጊዜ ከየመን፣ ሌላ ጊዜ ከቱርክ ፣ ሌላ ጊዜ ከግብፅ፣ በቅርብ ደግሞ ፋሽስት ኢጣሊያን ተገን አድርጎ ክርስቲያኖችን ያሰቃየ እና ማዕተብ ያስበጠሰ ማን እንደሆነ ይታወቃል። ሚዛናዊ የታሪክ ሊቃውንት ቢሆኑ ኖሮ ግራ ቀኙን መርምረው ሚዛናዊ ታሪክ ያቀርቡልን ነበር። የሠሩት ግን በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት እንደ ተባለው በመንግሥት በጀት እና በምርምር ስም የሚሠሩት ሌላ ነው፡፡
በአጠቃላይ የተዘጋጀው ጥራዝ ስሕተት የበዛበት በመሆኑ እንደገና ተስተካክሎ ሊቀርብ ይገባል። ለሀገርም ለትውልድም አሳቢ የሆኑ ምሁራን፣ ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ የሃይማኖት አባቶች ተወያይተውበት የጎደለው ሞልቶ፣ የተጣመመው ተስተካክሎ ተግባር ላይ መዋል እንዳለበት ማስገንዘብ እንፈልጋለን። ለወደ ፊትም ክፍተታችንን የሚሞላ እንጂ ይበልጥ እንድንለያይ እና በጥላቻ እንድንተያይ የሚያደርገንን ልቦለድ የታሪክ መጽሐፍ በማለት እንዳያቀርቡልን ምህራንን ማስገንዘብ እንፈልጋለን።