‹መኑ ውእቱ ገብር ኄር፤ ታማኝ አገልጋይ ማነው?››

በመ/ ምስጢረ ሥላሴ ማናየ
መጋቢት ፲፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስያሜ የዐቢይ ጾም ስድስተኛው እሑድ ወይም ሳምንት ‹ገብር ኄር› ይባላል፡፡ ሰያሜውን የሰጠውም ኢትዮጵያዊ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ ከአምስቱ መጻሕፍቶቹ አንዱ በኾነው ጾመ ድጓ መጽሐፍ ሳምንቱን የዐቢይ ጾም ሳምንታት ስያሜዎች ከነሥርዓተ ማኅሌቱ አዘጋጅቷል፡፡ ስለዚህ በስድስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ከዋዜማው ቅዳሜ ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን የሚዘመረው ዝማሬ፣ የሚሰበከው ስብከት፣ የሚሰጠው ትምህርት ገብር ኄርን የሚያወሳ ነው ማለት ስለ ታማኝ አገልጋይ የሚያስረዳ ነው፡፡ በማቴዎስ ወንጌል ፳፭፥፲፬-፳፭ የተገለጸውና በዕለቱ የሚነበበው ወንጌል የሚነግረንም ይህንኑ ትምህርት ነው፡፡
አንድ ባዕለ ጸጋ ሰው ባሪያዎችን ጠርቶ ለአንዱ አምስት መክሊት ሰጠው፣ ሁለት መክሊት የሰጠውም አለ፣ አንድ መክሊትም የሰጠው አለ፡፡ ከዚህ በኋላ ወደሩቅ አገር ሔደ፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለውም ወጥቶ ወርዶ ሌላ አምስት አትርፎ ዐሥር አደረገ፡፡ ሁለት የተቀበለውም አትርፎ አራት አደረገ፡፡ አንድ የተቀበለው ግን መሬቱን ቆፍሮ በሻሽ ጠቅልሎ የጌታውን መክሊት ቀበራት፡፡ ከብዙ ጊዜ በኋላ ጌታቸው መጥቶ ተቆጣጠራቸው፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለው ቀርቦ ‹‹ጌታዬ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር እነሆ አምስት አተረፍኩ›› አለው፡፡ ‹‹ገብር ኄር ወምዕመን ዘበውሁድ ምእምነ ኮንከ ዲበ ብዙህ እሰይመከ ባእ ውስተ ፍሥሐሁ ለእግዚእከ፤ አንተ ታማኝ ባሪያ! በጥቂቱ ታምነሃልበብዙ እሾምሃለሁ፡፡ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ!›› አለው፡፡ ሁለት የተቀበለውም ቀርቦ ‹‹ጌታዬ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር እነሆ ወጥቼ ወርጄ ሌላ ሁለት አትርፌ አራት አድርጌአለሁ፤›› ብሎ መክሊቱን አቀረበ፡፡ ጌታውም፡- ‹‹አንተ ታማኝ በጎ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃልበብዙ እሾምሃለሁ፡፡ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ!›› አለው፡፡
አንድ መክሊት የተቀበለው ግን ‹‹ጌታዬ፣ አንተ ክፉና ጨካኝ፤ ካልዘራህበት የምታጭድ፤ ካልበተንህበት የምትሰበስብ፤ እንደ ኾንክ ስለ አወቅሁ መሬቱን ቆፍሬ ቀበርኋት እነኋት መክሊትህ›› አለው፡፡ ‹‹አንተ ሰነፍ ባሪያ! መክሊቴን በጊዜ ልትሰጠኝ በተገባህ ነበር፡፡ እኔም ወጥቶ ወርዶ ለሚያተርፍ በሰጠሁት ነበር፤›› አለና ‹‹ኑ፤ የዚህን ሐኬተኛ መክሊት ውሰዱና ዐሥር መክሊት ላለው ስጡት፡፡ላለው ይሰጡታል ይጨመርለታል ለሌለው ግን ያለውን ይቀሙታል›፡፡ ንዑ ይህን ሰነፍና ሐኬተኛ ባርያ እጅ እግሩን አሥራችሁ ጽኑ ጨለማ ወደ አለበት ውሰዱት! ጩኸትና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ጨምሩት!›› የሚል ፍርድ ወሰነበት፡፡
ባዕለ ጸጋ የተባለው ጌታ ነው፡፡ መክሊት የተባለው ልዩ ልዩ የአገልግሎት ጸጋ ነው፡፡ ያተረፉት በሚገባ በታማኝነት ያገለገሉ ቅዱሳን ሰዎች ናቸው መክሊቱን የቀበረው ደግሞ በታማኝነት በተሰጠው ጸጋ ማገልገል ሲገባው ያላገለገለ ነው፡፡ ጌታቸው ሊቆጣጠራቸው መጣ ማለት ጌታችን በዕለተ ምጽአት ለዅሉም በሠራው ምግባር መጠን ዋጋ ለመስጠት እንደሚመጣ ያሳየናል፡፡ ያገለገሉትን ‹‹ወደ ጌታህ ደስታ ግባ!›› አላቸው ማለት ታማኝ አገልጋዮች መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉና፡፡ ሰነፉ አገልጋይ ወደ ጨለማና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ቦታ መወርወሩም ኀጥአን ወደ ሲኦል መግባታቸውን የሚያሳይ ነው፡፡
ከላይ ያነሳነው የቅዱስ ወንጌል ቃል፡- ‹‹ታማኝ አገልጋይ ማነው?›› ይላል፡፡ ይህ እያንዳንዱ በአርአያ እግዚአብሔር የተፈጠረ የሰው ልጅ ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህ አምላካዊ ጥያቄ ምላሽ መስጠት ከሰው ልጆች ይጠበቃል፡፡ ከዚህ ቀጥለን በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካቸው ከተመዘገበላቸው ታማኝ አገልጋዮች መካከል ሦስቱን ጠቅሰን ከእነርሱ ሕይወት እንድንማር የሚያነሣሣ መጠነኛ ትምህርት እናቀርባለን፤
ሙሴ
ሊቀ ነቢያት ሙሴ ታማኝ አገልጋይ መኾኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፤ ‹‹በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር እኔ እግዚአብሔር በራእይ እገለጥለታለሁ ወይም በሕልም አናግረዋለሁ፡፡ ባሪያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም እርሱ በቤቴ ዅሉ የታመነ ነው፤›› እንዲል (ዘኍ.፲፪፥፮)፡፡ ይህ የፍጡር ቃል ሳይኾን በፈጣሪው የተሰጠ ምስክርነት ነው፡፡ በውኑ በዘመናችን እንኳን ፈጣሪ ፍጡራን ታማኝነቱን የሚመሰክሩለት አጋልጋይ ይኖር ይኾን? እንጃ! የሙሴን ታማኝ አገልጋይነት በረኃ፣ ስደት፣ መከራ፣ የፈርዖን ግርማ እና ቁጣ አልበገረውም፡፡ ዐርባ ዓመት ስለ ወንድሞቹ በመሰደድ ዐርባ ዓመት ደግሞ የተሰደደላቸው ወንድሞቹን በመምራት፣ ባሕር በመክፈል፣ ጠላት በመግደል፣ መና በማውረድ፣ ደመና በመጋረድ ውኃ ከዓለት አፍልቆ በማጠጣት መከራውን ከወገኖቹ ጋር በመቀበል የቀኑን ኃሩር፣ የሌሊቱን ቁር (ብርድ) ታግሦ በታማኝነት አገልግሏል፡፡ ታማኝነቱም እስከ ሞት ድረስ ነበር፡፡
‹‹ሙሴም ወደ እግዚብሔር ተመልሶወዮ እኒህ ሕዝብ ታላቅ ኃጢአት ሠርተዋል፡፡ ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል፡፡ አሁን ይህን ኀጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍከው መጽሐፍ እባክህ ደምስሰኝ? ከባለሟልነትህ አውጣኝ?›› ተብሎ ተጽፏል (ዘፀ.፴፪፥፴፩)፡፡ ታማኝ አገልጋይ የሚባለው እንደ ሙሴ ‹‹እኔ ልሙት ሌሎች ይዳኑ›› የሚል ሰው ነው፡፡ አሁን የምናየው ግን ፈጽሞ ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ‹‹ሰዎች ይሙቱ፤ እኔ ልኑር፡፡ ሰዎች ጦም ይደሩ፤ እኔ ልብላ፡፡ ሰዎች ይራቆቱ፤ እኔ ልልበስ፡፡ ሰዎች ይዘኑ፤ እኔ ልደሰት›› ነው፡፡ ይህም ታማኝ አገልጋይ ያለ መኾን መገለጫ ነው፡፡ ታማኝ አገልጋይ ለሚያገለግላቸው ሰዎች ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ እንጂ የራሱን ጥቅም የሚያስቀድም አይደለም፡፡
ዛሬ በዓለማችን የምንመለከተው ድርጊት ግን ‹‹ጩኸት ለአሞራ መብል ለጅግራ›› የሚባለውን ዓይነት ነው፡፡ በታማኝ አገልጋዮች ድካም የሚሸለሙ፤ ታማኝ አገልጋዮች በሠሩት ሪፖርት የሚያቀርቡ፤ ባልሠሩት ሥራ የሚወደሱ፤ ከጥቅሙ እንጂ ከድካሙ መካፈል የማይሹ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ እንቅፋት የሚመታው እግርን ነው፡፡ አክሊል የሚቀዳጀው ግን ራስ ነው፡፡ ታማኝ አገልጋይ ማለት እንደራስ አክሊል ዘውድ የሚጸፋ ብቻ ሳይኾን እንደ እግር እንቅፋቱን፣ እሾኹን፣ ውጣ ውረዱን፣ መከራውንና ድካሙን የሚቀበል ነው፡፡ በጥቅም ጊዜ ለራሱ በአካፋ የሚዝቅ፤ ሌሎች በጭልፋ የሚቆነጥር አይደለም፡፡ ሙሴ ባሕር የከፈለው፣ መና ያወረደው ደመና የጋረደው ውኃ ያፈለቀው ለራሱ አልነበረም፤ ለሚመራቸው ሕዝብ ነበር እንጂ፡፡ ታማኝ አገልጋይ ያሰኘውም ይኸው ነው፡፡ በዚህ ከብሮበታል፤ ተመስግኖበታልም፡፡
ዳዊት
ነቢዩ ዳዊት ዘመነ መሳፍንት አልፎ ዘመነ ነገሥት ሲተካ እስራኤልን በንጉሥነት እንዲመራ እግዚአብሔር ከበግ ጥበቃ የመረጠው ንጉሥ ነው፡፡ እርሱም በተሰጠው ሥልጣን ሳይታበይ በታማኝነት ሕዝበ እስራኤልን መርቷል፡፡ እግዚአብሔር ለሙሴ እንደ መሰከረው ዅሉ ስለ ለዳዊትም መስክሮለታል፡፡ ‹‹እግዚአብሔር እንደ ልቡ የኾነ ሰው መርጧልናየዘይቱን ቀንድ ሞልተህ በልጆቹ መካከል ለእኔ ንጉሥ አዘጋጅቻለሁና ወደ እሴይ ወደ ቤተ ልሔም እልክሃለሁ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (፩ሳሙ. ፲፫፥፲፫፤ ፲፮፥፪)፡፡
በመዝሙረ ዳዊትም ‹‹ወረከብክዎ ለዳዊት ገብርየ ወቀባዕክዎ ቅብዐ ቅዱስ፤ ባሪያዬ ዳዊትን አገኘሁት የተቀደሰ ዘይትንም ቀባሁት›› ተብሎ ተነግሮለታል (መዝ. ፹፰፥፳)፡፡ ይህንንም አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በመጽሐፈ ሰዓታት ድርሰቱ፡- ‹‹ረከብክዎ ለዳዊት ገብርየ ብእሴ ምእመነ ዘከመ ልብየ፤ አገልጋዬ ዳዊትን እንደ ልቤ የታመነ ሰውን አገኘሁት›› ሲል ተርጕሞታል፡፡ ንጉሥ ዳዊት ከመንገሡ በፊት የተገኘው በታማኝነት ነበር፡፡ ከነገሠ በኋላም ታማኝ ነበር፡፡ አሁን በዚህ ዓለም የምንኖር እኛ ግን በድኅነት ታማኝ እንኾንና ሀብት፣ ሹመት፣ ሥልጣን ሲመጣ ታማኝነትን እናጣለን፤ እንዲያውም ታማኝነትን እንንቀዋለን፡፡ መስረቅ ጀግንነት ይመስለናል፡፡ መዋሸት ሥልጣኔ ይኾንልናል፡፡
ዳዊት ሳይሾም በጎቹን በመጠበቅ ታማኝ ነበር፡፡ በጎቹን የሚነጥቅ ተኩላ አንበሳ ቢመጣ በኋላው ተከትሎ ነብሩን በጡጫ፣ አንበሳውን በእርግጫ ብሎ በጎቹን ያስጥል ነበር፡፡ ‹‹እኔ ባሪያህ የአባቴን በጎች ስጠብቅ አንበሳ ወይም ድብ ይመጣ ነበር፡፡ ከመንጋውም ጠቦት ይወስድ ነበር፡፡ በኋላውም እከተለውና እመታው ነበር፤ ከአፉም አስጥለው ነበር፡፡ በተነሣብኝም ጊዜ ጉሮሮውን አንቄ እመታውና እገድለው ነበር፡፡ ይህም ፍልስጥኤማዊ ከነዚያ እንደ አንዱ ይኾናል፤ እንግዲህ እገድለው ዘንድ፤ ከእስራኤል ተግዳሮትን አስወግድ ዘንድ ዛሬ አልሔድምን? የሕያው አምላክ ጭፍሮችን ይገዳደር ዘንድ ይህ ቆላፍ ምንድን ነው? ከአንበሳና ከድብ ያስጣለኝ እግዚአብሔር ከዚህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያስጥለኛል!›› በማለት እርሱ እንደ ተናገረው (፩ኛሳሙ.፲፯፥፴፬)፡፡
ዛሬም ቢኾን በእስራኤል ዘነፍስ በምእመናን ላይ የሚገዳደሩ ብዙ ፍልስኤማውያን ተሰልፈዋል፡፡ እነዚህን ድል የሚነሣ፤ በጎቹን ምእመናን ከተኩላ፣ ከአንበሳና፣ ከድብ አፍ የሚታደግ ታማኝ አገልጋይ ማነው? ከምእመናን ተግዳሮት የሚያርቅ ፈጣሪዬ ከመከራ ያድነኛል ብሎ የሚታመን የኢ አማንያን ብዛት የማያስፈራው ማን ነው? ከትንሽነቱ እስከ ታላቅነቱ የታመነ አገልጋይ ማነው? ለተሾመበት ሓላፊነት ታማኝ ማነው? አሁንም ዓለማችን ከሥጋውያን ባለ ሥልጣናትም ኾነ ከመንፈሳውያን መሪዎች የምትሻው ታማኝ ሰው ነው፡፡ በሙስና ያልተዘፈቀ፤ ጉቦ አይኑን ያላጨለመበት፤ ለመንጋው አርአያና ምሳሌ የሚኾን ሰው፤ ታማኝ አገልጋይ ማለት እርሱ ነው፡፡ በመሐላ የተቀበለውን የአገልግሎት ሓላፊነት የማይዘነጋ ጳጳስ፣ ቄስ፣ ዲያቆን፣ ሰባኪ፣ መምህር፣ ሐኪም፣ ዳኛ፣ ነጋዴ፣ ተማሪ፣ ወታደር፣ የቤት ሠራተኛ፣ የቢሮ ሠራተኛ ታማኝ መኾን አለበት፡፡
መንጋው በክህደት ሲጠፋ ዝም ብሎ የሚያይ ጳጳስ፣ ቄስ፣ ዲያቆን፣ መምህር፣ ሰባኪ፣ ታማኝ አይደለም፡፡ ታማሚው እየተሰቃየ የሚዝናና ሐኪም ታማኝ አይደለም፡፡ ፍርድ የሚያጎድል፤ ድሆችን የሚበድል፤ ለደሃ አደጎች የማይፈርድ ዳኛ ታማኝ አገልጋይ አይደለም፡፡ ቅቤ በሙዝ እና በድንች ቀላቅሎ፣ በርበሬ በሸክላ አፈር ጨምሮ፣ ሌሎችን አጭበርብሮ የሚሸጥ ነጋዴ ታማኝ አገልጋይ አይደለም፡፡ እየነገደ ያለው በሰው ሕይወት መኾኑን መዘንጋት የለበትም፡፡ ዅሉም እንደየአቅሙ በተሰጠው የአገልግሎት ዘርፍ ታማኝ መኾን አለበት፡፡
ዮሴፍ
ዮሴፍ ለወንድሞቹ ምግባቸውን ተሸክሞ የእርሱ ስንቅ ቢያልቅ የወንድሞቹን ስንቅ ያልበላ በትንሹ የታመነ ሰው ነበር፡፡ ወንድሞቹ ሸጠውት በቤተ ጲጥፋራ በሚያገለግልበት ጊዜም ታማኝ ነበር፡፡ ታማኝነቱ በጲጥፋራ ቤት ጌታ አድርጎታል፡፡ ‹‹ዮሴፍ ተሸጠአገልጋይም ኾነ፡፡ እግሮቹ በእግር ብረት ሰለሰሉ፡፡ ሰውነቱም ከብረት አመለጠች፡፡ ቃሉ ሳይደርስ የእግዚአብሔር ቃል ፈተነው፡፡ ንጉሥ ላከ፤ ፈታውም የሕዝብ አለቃ አድርጎ ሾመው፡፡ የቤቱም ጌታ አደረገው፡፡ በገንዘቡ ዅሉ ላይ ገዢ አደረገው፡፡ አለቆቹን እንደ እርሱ ይገሥፅ ዘንድ፤ ሽማግሌዎችን እንደ እርሱ ጥበበኞች ያደርጋቸው ዘንድ፤›› ተብሎ እንደ ተነገረለት (መዝ.፻፬፥፲፯)፡፡
በዚህ ኹኔታ የነበረው ዮሴፍ የጌታው ሚስት ሲወጣ ባቱን፣ ሲገባ ደረቱን እያየች ዐይኗን ጣለችበት፤ በዝሙት አይን ተመለከተችው፡፡ ‹‹ከእኔ ጋር ተኛ›› እያለችም በየቀኑ አስቸገረችው፡፡ እርሱ ግን ‹‹እምቢ›› አላት፡፡ ለጌታው ሚስትም፡- ‹‹እነሆ ጌታዬ በቤቱ ያለውን ዅሉ ለእኔ በእጄ አስረክቦኛል፡፡ በቤቱ ያለውን ምንም የሚያውቀው የለም፡፡ በዚህ ቤት ከእኔ የሚበልጥ ሰው የለም፡፡ ሚስቱ ስለ ኾንሽ ከአንቺ በቀር ያልሰጠኝ ነገር የለም፡፡ እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ? እንዴትስ በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአትን እሠራለሁ?›› በማለት የዝሙት ጥያቄዋን ውድቅ አደረገባት (ዘፍ.፴፱፥፯)፡፡
በዮሴፍ ታማኝነት የጌታው ቤት ተባርኳል፡፡ ሀብቱ በዝቷል፡፡ በታማኝነቱ በቤቱ ያለውን ዅሉ ተረክቦ ነበር፡፡ የቀረበለት ፈተና ግን ከባድ ነበር፤ ኾኖም ግን በታማኝነቱ ለማለፍ ችሏል፡፡ ዮሴፍ በታማኝ አገልጋይነቱ በመጣበት መከራ ቢታሰርም እንኳን ያለ ሹመት አላደረም፤ የእስረኞች አለቃ ነበር፡፡ ከእስር ቤት ሲወጣም ግብጽን በሙሉ መርቷል፡፡ በግብጻውያን ላይ ተሾሟል፤ በጥቂቱ ታምኗልና፡፡ ‹‹በጥቂቱ የታመነ በብዙ ይሾማል›› እንዲል (ማቴ.፳፭፥፳፬)፡፡ዛሬ በእየአንዳንዱ ጓዳ እንደ እሳት የሚያቃጥሉ አገልጋዮች ናቸው ያሉት፡፡ ልጅ በፈላ ውኃ የሚቀቅሉ ናቸው የሚበዙት፡፡ እንኳን በዅሉ ገንዘብ ለመሾም በጥቃቅን ዕቃዎች እንኳን የሚታመን ሰው ጠፍቷል፡፡ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ፡- ‹‹አቤቱ አድነኝ፤ ደግ ሰው አልቋልና፡፡ ከሰው ልጆችም መተማመን ጎድሏልና፤›› በማለት እንደ ተናገረው በመካከላችን መተማመን የለም (መዝ.፲፩፥፩)፡፡
እናም ከእነዚህ ሦስት ታማኝ አገልጋዮች (ሙሴ፣ ዳዊት እና ዮሴፍ) ሕይወት ዅሉም የሰው ልጅ ታማኝ አገልጋይነት የሚያሰጠውን ክብርና ጸጋ ተመልክቶ በታማኝነት ማገልገል ይገባዋል፡፡ ታማኝ መኾን መጀመሪያ የሚጠቅመው ራስን ነው፤ ከዚያ በኋላ ለአገር፣ ለወገን፣ ለቤተ ክርስቲያን፣ ላመኑትም ላላመኑትም ዅሉ ጠቃሚ ይኾናል፡፡ በመጨረሻም የጽድቅ አክሊልን ይቀዳጃል፤ መንግሥተ ሰማያትን ያወርሳል፡፡ ታማኝነት በሰውም፣ በእግዚአብሔርም ፊት ያስከብራልና፡፡ ጻድቃን፣ ሰማዕታት ቅዱሳን በታማኝነት በማገልገላቸው ፈጣሪአቸውን ደስ አሰኝተው ከብረዋል፡፡
በሓላፊው ገንዘብ ያልታመኑት እነይሁዳ፣ ሐናንያ እና ሰጲራ የደረሰባቸውን ጉዳት አይተናል፡፡ አካን ወልደ ከርሚንም ተመሳሳይ ቅጣት ደርሶበታል (ሐዋ.፭፥፩-፳፭)፡፡ ስለ ኾነም ዅሉም በተሰማራበት የአገልግሎት መስክ ታማኝ አገልጋይ ኾኖ ‹‹አንተ በጎ ታማኝ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃል፤ በብዙ እሾምሀለሁ፤›› የሚለውን የጌታውን የምስጋና ቃል ለመስማት ተዘጋጅቶ መጠበቅ ይገባዋል፡፡ መልካም አገልግሎት አገልግለን፣ በእግዚአብሔር ‹አግብርት ኄራን፤ ታማኝ አገልጋዮች› እንድንባል፤ መንግሥቱንም እንድንወርስ አምላካችን ይርዳን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ወረደ መንፈስ ቅዱስ

ሰኔ ፲፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም
በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው
መንፈስ ቅዱስ ማለት ከሦስቱ አካላት (ከቅድስት ሥላሴ) አንዱ፤ የእግዚአብሔር አብ፣ የእግዚአብሔር ወልድና የራሱም አካላዊ እስትንፋስ የኾነው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡
*ወረደ መንፈስ ቅዱስ* የሚለው የግእዝ ዓረፍተ ነገርም *መንፈስ ቅዱስ ወረደ* የሚል ትርጕም ያለው ሲኾን፣ ይህ ሲባልም በሰዉኛ ቋንቋ ከከፍታ ወደ ዝቅታ፣ ከሩቅ ወደ ቅርብ መምጣቱን ወይም መውረዱን ሳይኾን የእግዚአብሔር መንፈስ በሐዋርያት ላይ አድሮ ሰማያዊ ሀብትን፣ ዕውቀትን፣ ጥበብን መግለጹንና ልዩ ልዩ ጸጋን ማደሉን ያመላክታል፡፡
ይህ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ለጊዜው ለሐዋርያት ቢሰጥም፣ በእነርሱ ላይ ብቻ ሳይገደብ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ በምእመናን ላይም አድሮ ይኖራል፡፡
ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ ወረደ የሚለው ትምህርት መንፈስ ቅዱስን በቦታ፣ በጊዜና በወሰን መገደቡን አያመለክትም፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ በዓለሙ ኹሉ የሞላ ነውና፡፡ በሰው ላይ አድሮ ጥበብን ሲገልጽ ግን ሞላ፤ አደረ፤ ወረደ ተብሎ ይነገራል፡፡ ይኸውም ሥራዉን በሰው ላይ መግለጡን፣ ጸጋዉንም ማብዛቱን ለማመልከት የሚያገለግል ቋንቋ ነው፡፡
ከላይ እንደ ተገለጸው እግዚአብሔር በቅዱሳን ሐዋርያት ላይ ፍርኃትን አስወግዶ ጥብዓትን (ጭካኔን)፣ ስጋትን አጥፍቶ ቈራጥነትን (ድፍረትን) ማሳደሩን፤ እንደዚሁም ሰማያዊ ሀብትን፣ ዕውቀትን፣ ጥበብንና ጸጋን እንዲያገኙ ማድረጉን፤ በዚህም ሐዋርያት ለስብከተ ወንጌልና ለሰማዕትነት የሚያበቃ ቅድስና ላይ መድረሳቸዉን ያመለክታል፡፡
መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ የወረደው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደባት፣ በተጠመቀባትና ከሞታን ተለይቶ በተነሣባት በዕለተ ሰንበት (በሰንበት ክርስቲያን) ሲኾን፣ መንፈስ ቅዱስ ከወረደበት ሰንበት (ከኀምሳኛው ቀን) ጀምሮ እስከሚቀጥለው ሰንበት ያለው ጊዜም (ስምንቱ ቀናት) ዘመነ ጰራቅሊጦስ ወይም ሰሙነ ጰራቅሊጦስ ይባላል፡፡ ይህም መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ ስለ መውረዱና በምእመናን ላይ ስለ ማደሩ የሚነገርበት ወቅት ነው፡፡
በዚህ ሰሙን በቤተ ክርስቲያን የሚነገረው ቃለ እግዚአብሔር፣ የሚሰጠውም ትምህርት የመንፈስ ቅዱስን በሐዋርያት ላይ መውረድ የሚመለከት ነው፡፡ ስለዚህም ከኀምሳኛው ቀን (ከበዓለ ጰራቅሊጦስ) ቀጥሎ በሚመጣው እሑድ (በስምንተኛው ቀን) በሌሊት በሊቃውንቱ የሚዘመረው መዝሙር፡- *ወረደ መንፈስ ቅዱስ ላዕለ ሐዋርያት ከመ ዘእሳት ወተናገሩ በነገረ ኵሉ በሐውርት* የሚል ሲኾን፣ ትርጕሙም መንፈስ ቅዱስ በእሳት አምሳል በሐዋርያት ላይ መውረዱንና በእርሱ ኃይል በዓለሙ ኹሉ ቋንቋዎች መናገራቸዉን የሚያስረዳ ነው፡፡
በዚህ ዕለት በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም፡- የሚከተሉት ናቸው፤ ኤፌ.፬፥፩-፲፯፤ ፩ኛዮሐ.፪፥፩-፲፰፤ ሐዋ.፪፥፩-፲፰፤ መዝ.፷፯፥፲፰ (ምስባክ)፤ ዮሐ.፲፬፥፩-፳፪ (ወንጌል)፡፡
የምንባባቱ ፍሬ ዐሳብም የጳውሎስ መልእክት፡- እያንዳንዳችን መንፈስ ቅዱስ በገለጸልን መጠን የየራሳችን ልዩ ልዩ ጸጋ እንዳለን፤ የዮሐንስ መልእክት፡- የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ለዘለዓለም ሕያው እንደ ኾነ፤ የሐዋርያት ሥራ፡- መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ እንደ ወረደና በዓለሙ ኹሉ ቋንቋዎች መናገር እንደቻሉ፤ መዝሙረ ዳዊት (ምስባኩ)፡- እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ልዩ ልዩ ጸጋን እንደሚሰጥ፤ የዮሐንስ ወንጌል፡- እግዚአብሔር እኛን ልጆቹን እንደ ወላጅ አልባ እንደማይተወን ያስረዳሉ፡፡
ቅዳሴውም ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ ሲኾን፣ ይህም ምሥጢረ ሥላሴን፣ የጌታችንን ሰው መኾን፣ ሕማሙን፣ ሞቱን፣ ትንሣኤዉን፣ ዕርገቱንና መንፈስ ቅዱስን መላኩን ይናገራል፡፡
ቅድስት በኾነች በጽርሐ ጽዮን በሐዋርያት ላይ የወረደው የእግዚአብሔር አብ ጸጋ፣ የእግዚአብሔር ወልድ ፍቅር፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድነት በኹላችን ላይ ይደር፤ እጽፍ ድርብም ይኹን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ጰራቅሊጦስ ከሣቴ ምሥጢር

ሰኔ ፲፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም
በመምህር ማዕበል ፈጠነ
ጰራቅሊጦስ ማለት ከሣቴ ምሥጢር ማለት ነው፡፡ ይኸውም በግብሩ ታውቋል፡፡ በበዓለ ጰራቅሊጦስ አበው ሐዋርያት ብዙ ምሥጢር በመንፈስ ቅዱስ ተገልጾላቸው ብሉይና ሐዲስን ተርጕመዋል፡፡
ማለትም ወደ ኋላ ተመልሰው *እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በመጨረሻው ቀን ሥጋ በለበሰ ኹሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፡፡ ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤* ተብሎ የተነገረውን ትንቢት ጠቅሰው፣ በመብረቅ መጽሔት ተሞልተው ወደ ፊት የሰው ልጅ በሃይማኖትና በምግባር የሚወርሳትን የመንግሥተ ሰማይን ተስፋ አብሥረዋል /ሐዋ.፪፥፲፯፤ ኢዩ.፪፥፲፰/፡፡
ከቀደመው ቋንቋቸው ሌላ ፸፩ ቋንቋ ተገልጾላቸው በ፸፪ ቋንቋ አስተምረዋል፡፡ ይህ ሲባል ግን በዘመኑ የነበረው ሕዝብ እርስበርስ ይግባባቸው የነበሩት ቋንቋዎች ፸፪ ስለ ነበሩ ነው እንጂ መንፈስ ቅዱስ ከዚህም በላይ ቋንቋዎችንና ጥበብን መግለጽ እንደሚቻለው ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ጥንተ ነገሩስ እንደምን ነው ቢሉ ጌታችን በዚህ ዓለም ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ወንጌለ መንግሥትን አስተምሮ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ፣ በሲኦል የነበሩ ነፍሳተ ሙታንን ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ አውጥቶ የሲኦልን በር ዘግቷል፡፡
በዚህ ዓለም ደግሞ ብርሃነ መለኮቱን ገልጾ ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ፵ ቀን ለአበው ሐዋርያት በመጽሐፈ ኪዳን የተገለጹ ረቂቅ ምሥጢራትን አስተምሮ መንፈስ ቅዱስ ትርጕሙን እንደሚነግራቸው፤ በሰዓቱ ግን መሸከም እንደማይችሉ ነግሯቸው ባረገ በ፲ኛው ቀን ለ፲፪ቱ ሐዋርያት፣ ለ፸፪ቱ አርድእትና ለ፴፮ቱ ቅዱሳት አንስት በአጠቃላይ ለ፻፳ው ቤተሰብ መንፈስ ቅዱስን ልኮላቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ በአዲስ ልሳን መናገር ጀምረዋል፡፡
አዲስ ልሳን ሲባልም በዓለም የሌለ ሌላ ባዕድ ቋንቋ ማለት አይደለም፡፡ የዓለም ቋንቋዎች ኹሉ በመንፈስ ቅዱስ እሳትነት በሐዋርያት አንደበት ተዋሐዱ፤ በልቦናቸው አደሩ፤ ሐዋርያት በዕውቀት ታነፁ ማለት ነው እንጂ፡፡ እንደሚታውቀው የሰው ልጅ የዓለማትን ቋንቋ በሙሉ ተምሮ ለማወቅ አይቻለዉም፡፡ አበው ሐዋርያት ግን ከሥጋዊ፣ ከደማዊ መምህር በመማር፤ መልክአ ፊደል በማጥናት ሳይኾን፣ መንፈስ ቅዱስ ገልጾላቸው አንደበታቸው ሰይፍ፣ ልሳናቸው ርቱዕ፣ ኾኖ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች መናገር ችለዋል፡፡
ነገር ግን ሐዋርያት ባዕድ ቋንቋ አላመጡም፡፡ ጌታም የገለጸላቸው የዚህ ዓለም ብርሃን እንደመኾናቸው በዓለም የሚነገሩ ቋንቋዎችን ነው፡፡ ሰው የማይሰማውን ቋንቋ ቢናገሩ ኖሮ ከነፋስ ጋር እንደመናገር ይቈጠር ነበር /፩ኛቆሮ.፲፬፥፱/፡፡ ይህንንም ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ *ወአኀዙ ይንብቡ ዘዘዚአሆሙ በነገረ ኵሉ በሐውርት በከመ ወሀቦሙ መንፈስ ቅዱስ፤ ኹሉም መንፈስ ቅዱስን ተሞሉ፡፡ ይናገሩ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እንዳደላቸው መጠንም እየራሳቸው በአገሩ ኹሉ ቋንቋ ይናገሩ ጀመሩ፤* በማለት ገልጾታል /ሐዋ.፪፥፬/፡፡
በዚህ ጊዜ ቤተ አይሁድ በከፊል አንጎራጎሩ፤ አሕዛብ ተደመሙ፡፡ ሐዋርያትን በገዛ ቋንቋቸው ሲናገሩ ሰምተው *እኛ የጳርቴ፣ የሜድ፣ የኢላሜጤም ሰዎች ስንኾን፣ በእኛ ቋንቋ እነሆ የእግዚአብሔርን ጌትነት ሲናገሩ እንሰማዋቸዋልን* ሲሉ አደነቁ፤ ከእግራቸው ሥርም ወደቁ፡፡ በቅፅበትም ሦስት ሺህ ነፍሳት አምነው ተጠመቁ፡፡
በዚህ ዘመን በግላቸው ቤተ እምነት መሥርተው የሚኖሩ ባዕዳን *መንፈስ ቅዱስ ወረደልን፤ አዲስ ልሳን ተገለጠልን፤ እልል በሉ፤* እያሉ ዐይናቸውን ይጨፍናሉ፤ አእምሯቸውን ይስታሉ፡፡ በአንደበታቸውም እነርሱ የማያውቁትን፤ ሌላ ሰውም ሊሰማው የማይችለዉን ትርጕም የሌለዉን ጩኸት፣ እነርሱ ልሳን የሚሉትን ድምፅ ያነበንባሉ፡፡
የመንፈስ ቅዱስ ዓላማ ሰዎች እርስበርስ እንዲግባቡ ትርጕም ያለዉን ቋንቋ መግለጽ እና ኹሉም በየቋንቋው የእግዚአብሔርን የምሥራች ቃል እንዲማር፣ እንዲያውቅና እንዲረዳ ማድረግ ነው፡፡ ልሳን ማለትም ሰው ሊረዳውና ሊግባባት የሚችል ቋንቋ ማለት እንጂ ድምፅ በማውጣት ብቻ የሚገለጽ ጩኸት አይደለም፡፡ መናፍቃኑ ልሳን የሚሉት ግን ይህንኑ ዓይነት ባዶ ጩኸት ነው፡፡ ይህም ከሰይጣን እንጂ ከመንፈስ ቅዱስ እንዳልኾነ ያጠይቃል፡፡
የመንፈስ ቅዱስ የሆነው አዲስ ልሳን ግን ትናንት በአበው ሐዋርያት ዘመን የነበረ፤ ዛሬም በእኛ ዘመን ያለ፤ ለመጭው ትውልድም የሚተላለፍ ሕያው ልሳን ነው፡፡ ለምን ቢሉ ከሣቴ ምሥጢሩ (ምሥጢር ገላጩ) መንፈስ ቅዱስ ነውና፡፡
እንግዲህ በነቢያት የተነገረው፣ በሐዋርያት ልቡና በእሳት አምሳል የተገለጠው ምሥጢረ መንፈስ ቅዱስ ይህ ነው፡፡ ይህ ምሥጢር ከትውልድ ወደ ትውልድ ተላልፎ በሐዋርያት ልቡና ቀርቷል፤ ከሐዋርያት ልቡና ያልደረሰው ደግሞ በልበ መንፈስ ቅዱስ ቀርቷል፡፡ ዓውደ ትምህርቱ ይህ ነው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

‹‹አንተ በጎና ታማኝ አገልጋይ›› ማቴ:25

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ 
ህዳር 15 ቀን 2007 ዓ᎐ም
ልዑል እግዚአብሔር አምላካችን በክቡር ዳዊት አድሮ፤ “እከሥት በምሳሌ አፉየ፤ ወእነግር አምሳለ ዘእምትካት፤ አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤ ከቀድሞ ጀምሮ ያለውንም ተምሳሌት እናገራለሁ” ብሏል፡፡ /መዝ. 77፡2/
በዚሁ መሠረት ጌታችን ወንጌለ መንግሥተ ሰማያትን በልዩ ልዩ ምሳሌ አስተምሯል፤ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 25 ሁለት ምሳሌያትና አንድ ትንቢት ቀርበዋል፡፡

 ከምሳሌያቱ የመጀመሪያው በዐሥሩ ደናግል አንጻር የቀረበው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ወጥተው ወርደው ነግደው ያተርፉበት ዘንድ ገንዘቡን ስለሰጠ ነጋዴ የሚናገረው ነው፡፡ ትንቢቱም ስለ ኅልቀተ ዓለም የተነገረ ነው፡፡ እንግዲህ በዚህ ዕትማችን ነግደው እንዲያተርፉበት ከጌታቸው የተሰጣቸውን መክሊት ስለተቀበሉት አገልጋዮች እንመለከታለን፡፡ ፈጣሪያችን ለብዎውን ማስተዋሉን ያድለን፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ያስተማራቸውን ምሳሌያዊ ትምህርቶችን በሰፊው ተጽፎ እናገኛለን፡፡
የእነዚህ ትምህርታዊ ምሳሌዎች መሠረታዊ ሀሳብና ዓላማ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምናገኝበትን የታማኝነትን ሥራን እንዴት መሥራት እንደሚገባንና እንደምንችል ማስተማር ነው፡፡
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ መንግሥተ ሰማያት ምሥጢር ያስተማራቸው ብዙ ምሳሌዎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ብዙ ምሳሌዊ ትምህርቶች መካከል በማቴዎስ ወንጌልም 25 ላይ እንዲያተርፉበት መክሊት ስለተሰጣቸውና ወጥተው ወርደው ሌላ አትረፈው በጌታቸው ስለተመሰገኑት ቸርና መልካም አገልጋዮች፣ እንዲሁም መክሊቱን በመቅበሩ ምክንያት በጌታው ስለተወቀሰውና ፍርድን ስለተቀበለው ሰው ታሪክ፣ የታሪኩም ምሥጢር ምን እንደሚመስል ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ምሳሌ የተናገረው በሚከተለው መልኩ ነበር ‹‹ወደ ሌላ ሀገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና ለእንዳንዱ እንደ ዓቅሙ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ ሀገር ወዲውኑ ሄደ፡፡ አምስት መክሊትም የተቀበለው ሄደ ነገደበት ሌላም አምስት አተረፈ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ፡፡ አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቆፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ፡፡
ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው፡፡

አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ፡- ጌታ ሆይ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፡ እነሆ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት አለ፡፡ ጌታውም፡- መልካም አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ:: ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡ ሁለት መክሊት የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፡- ጌታ ሆይ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፡፡ እነሆ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁበት አለ፡፡ ገታውም፡- መልካም አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ:: ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡
አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፡- ጌታ ሆይ ካልዘራህበት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት እነሆ መክሊትህ አለህ አለው፡፡ ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው፡- አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ ካልዘራሁበት እንዳጭድ ካልበተንሁባትም እንድሰበስብ ታውቃለህን:: ስለዚህ ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ልትሰጠው በተገባህ ነበር:: እኔም መጥቼ ያለኝን ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር፡፡ ስለዚህ መክሊቱን ውሰዱበት አሥር መክሊትም ላለው ስጡት::

ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና ይበዛለትማል:: ከሌላው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል፡፡ የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት:: በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል፡፡›› የሚል ነው፡፡ መክሊት ጥንት የክብደት መለኪያ ነበር:: አንድ መክሊት 30 ኪሎ ግራም ያህል ነው፡፡ በዚህ ምሳሌ ላይ እንደተገለጸውም መክሊት የሚለው ቃል ገንዘብን ያመለክታል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምሳሌ ውስጥ እርሱን የምናገለግል ሁላችን አንደየዓቅማችን ማድረግ የሚገባንን መንፈሳዊ የአገልግሎት ሥራንና በአገልግሎታችን ውጤታማ በመሆናችንም ከእርሱ የምናገኘውን ዘላለማዊ ክብርና ዋጋን እንዲሁም መሥራት የሚገባንን ባለማድረጋችንም ምክንያት የሚገጥመንን መለኮታዊ ቅጣትን አመልክቶናል፡፡ በዚህ ምሳሌ ውስጥ ባለ አምስት የተባለው ፍጹም ትምህርት ተምሮ ሌላውን መክሮ አስተምሮ ራሱን አስመስሎ ያወጣነው፡፡

በተመሳሳይም ባለሁለት የተባለው ፍጹም ትምህርት ተምሮ ሌላውን መክሮ አስተምሮ ራሱን አስመስሎ ያወጣ ሲሆን ባለአንድ የተባለው ደግሞ ተምሮ ሳያስተምር የቀረ ሰው ነው፡፡ በመሆኑም ባለአምስትና ባለሁለት መክሊት የሆኑት ወጥተው ወርደው ደክመው’ መከራ መስቀልን ሳይሰቀቁና ሳይፈሩ’ ነፍሳቸውን ለታመነው አምላክ አደራ በመስጠት የተማሩትን ፍጹም ትምህርት ለሌላው አስተምረው ሌላውን አንደራሳቸው የተማረ አድርገው ሲያወጡ ባለአንድ የተባለው ግን አላውያን እሳት ስለት አሳይተው ቢያስክዱኝ መናፍቃን ተከራክረው ምላሽ ቢያሳጡኝ ብሎ ፈርቶ ሃይማኖቱን በልቡ ከመያዝ በቀር የተማረውን ትምህርት ለሌላው ሊያስተምርና የተሰጠውን አደራንም ሊወጣ አልወደደም፡፡
በምሳሌው ውስጥ እንደተገለጠው ሌላ አምስትና ሁለት ያተረፉት በተሰጣቸው መክሊት ሌላ ማትረፋቸውን ለጌታቸው በገለጡ ጊዜ የመክሊቱ ባለቤት እጅግ አድርጎ እንዳመሰገናቸው ከላይ አንብበናል፡፡
ይህ የመክሊቱ ባለቤት የተባለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለተወጡት ሁሉ እርሱ ፍጹም ዋጋን የሚሰጣቸው መሆኑን ያመለክታል፡፡ ይህም ሁኔታ ‹‹ መልካም አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሃለሁ፡፡ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ›› በሚል ተገልጧል፡፡ ይህ ቃል በሃይማኖት ለእግዚአብሔር የታመኑ ሁሉ ወደ ፍጹም ደስታ ወደ መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ለሚያደርጉት ጉዞ እጅግ ተስፋ የሆነ ቃል ነው፡፡

በዚህ ላይ እንደተገለጸው እግዚአብሔር አምላክ ለሁላችንም እርሱን የምናገለግልበትንና ለእርሱ በመታመን ዘላለማዊ ክብርን የምናገኝበትን ዕውቀትን ማስተዋልን’ ሀብትን’ ዓቅም ወይም ጉልበትን ሌሎችንም ልዩ ልዩ ስጦታዎችን ለእኛ ለሰው ልጆች እንደየዓቅማችን መጠን ሰጥቶናል፡፡
እነዚህ ሁሉ ነገሮች የሥጋችንን ምኞት እንድንወጣባቸው የተሰጡ ሳይሆኑ ነፍሳችን የምትከብርበትን መልካም ሥራን የምንሠራባቸው ናቸው፡፡
በመሆኑም እርሱ በሰጠን የአገልግሎት ጸጋ በታማኝነት በማገልገል በተሰጠን ነገር ሁሉ መንፈሳዊውን ሀብት የምናተርፍ ልንሆን ይገባናል፡፡ ምክንያቱም እኛ የተጠራ ነው ፍሬ ልናፈራና ሌላውንም ልናተርፍ መልካም ሥራን ልንሠራ እንጅ የሥጋችንን ፈቃድ በመከተል የኃጢኣት ባሮች ልንሆን አይደለም፡፡
ከላይ እንደተመለከትነው በልዑል አምላክ በእግዚአብሔር አንደበት አንተ በጎ ታማኝ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ መባልን የመሰለ አስደሳችና አስደናቂ ነገር የለም፡፡ ይህ ደግሞ የሚገኘው ሃይማኖትን በሥራ በመግለጥ እንጅ ሃይማኖትን በልቦና በመያዝ ብቻ አይደለም፡፡ ከእነዚህም እንደ አቅማቸው መክሊት ተሰጥቷቸው ሌላ መክሊት ካተረፉት በጎና ታማኝ አገልጋዮች ከተባሉት የምንማረው እውነታ ይህ ነው፡፡ ስለዚህም በብዙ ለመሾም በጥቂቱ መታመን ግድ ነው፡፡
አንድ መክሊት የተሰጠውን ሰው ስንመለከተው ጌታውን ጨካኝ አድርጎ ከመቁጠር ውጪ በተሰጠው መክሊት ወጥቶ ወርዶ ሊያተርፍ አልወደደም፡፡ መክሊቱንም ባስረከበ ጊዜ በጌታው ላይ የተናገራቸው ቃላት የእርሱን አለመታዘዝና አመጸኝነት ይገልጡ ነበር፡፡

በመሆኑም ይህ ሰው በጥቂቱ መታመን ያቀተውና በአስተሳሰቡ ደካማነት እጅግ የተጎሳቆለ ሰው ነው፡፡ በዚህ ምሳሌ መሠረት ይህ ባለአንድ የተባለው ሰው ዓላውያን እሳት ስለት አሳይተው ቢያስክዱኝ መናፍቃን ተከራክረው መልስ ቢያሳጡኝ በማለት ሃይማኖቱን በልቡ ሸሽጎና ቀብሮ ከመያዙ ባሻገር በጌታ ፊት በድፍረት ቆሞ አንተ ሕግ ሳትሠራ በአዕምሮ ጠባይዕ አውቃችሁ’ መምህርም ሳትሰጥ በሥነ ፍጥረት ተመራምራችሁ በሠራችሁ ብለህ የምትፈርድ ጽኑ ጨካኝ መሆንክን አውቃለሁና ዓላውያን እሳት ስለት አሳይተው ቢያስክዱኝ መናፍቃን ተከራክረው መልስ ቢያሳጡኝ ብየ ፈርቼ ሃይማኖቴን በልቡናየ ይዠዋለው በአዕምሮየ ጠብቄዋለሁ የሚል ሃይማኖቱን ግን በሥራ የማይገልጥ ሰነፍ ሰውን ያመለክታል፡፡
ለዚህ ዓይነት ሰው የጌታ መልስ ደግሞ በምሳሌው መሠረት የሚከተለው ነው፡፡ እኔ ሕግ ሳልሠራ በአዕምሮ ጠባይዕ አውቃችሁ መምህር ሳልሰጥ በሥነ ፍጥረት ተመራምራችሁ አውቃችሁ በሠራችሁት ብየ የምፈርድ ጽኑ ጨካኝ መሆኔን ታውቃለህን? እንዲህስ ካወቅህ ሹመትክን ልትመልስልኝ ይገባኝ ነበር፡፡ ወጥቶ ወርዶ ለሚያስተምር በሰጠሁት ነበር፡፡ አሁንም የእርሱን መምህርነት ሹመት ነሥታችሁ (ወስዳችሁ) ለዚያ ደርቡለት! እርሱን ግን አውጡት የሚል ነው፡፡ ዛሬም እያንዳንዳችን በዓቅማችን መጠን መክሊት ተሰጥቶናል፡፡ በመሆኑም መክሊቱን እንደቀበረው እንደዚያ ሰው የተሰጠንን ቀብረን ለወቀሳና ለፍርድ እንዳንሰጥ በአገልግሎታችን ልንተጋ ይገባናል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንኑ ሲገልጥ ‹‹አገልግሎት ቢሆን በአገልግሎታችን እንትጋ የሚያስተምርም በማስተማሩ ይትጋ የሚሰጥም በልግሥና ይስጥ›› (ሮሜ12፥7) በማለት ተናግሯል፡፡ ለመሆኑ ዛሬ ‹‹አንተ በጎ ታማኝ አገልጋይ…›› ተብሎ በእግዚአብሔር ሊመሰገን የሚችል ማን ይሆን? በእውነት በዘመናችን እንዲህ ተብሎ የሚመሰገን በጎና ታማኝ ካህን’ ታማኝ መምህርና ሰባኪ’ ታማኝ ዘማሪ የመሳሰለውን ማግኘት ይቻል ይሆንን? ትልቅ መሠረታዊ ሊሆን የሚገባው ጥያቄ ቢኖር ይህ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ስለ ታማኝነት የሁላችንንም ሕይወት የሚዳስስና ሁላችንንም የሚመለከት ነውና፡፡

በእርግጥም ዛሬም ቢሆን እንደ አባቶቻችን ማለትም እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት በእምነት’ በትዕግስት በፍቅር’ በትህትናና በትጋት በማገልገል የተሰጣቸውን መክሊት የሚያበዙ አገልጋዮች አሉ፡፡ የእነዚህ ክብራቸው በምድርም በሰማይም እጅግ የበዛና ራሳቸውን አስመስለው በትምህርት የወለዷቸው ልጆቻቸውም ለቤተክርስቲያን ውድ ልጆች ናቸው፡፡
ለምሳሌ ቅዱስ ጴጥሮስ ቀሌምንጦስን’ ቅዱስ ጳውሎስም ጢሞቴዎስን አፍርተዋል፡፡

ሌሎችም አበው ቅዱሳን በወንጌል ቃል መንፈሳውያንና ትጉሃን የሆኑ ምእመናንን በሚገባ አፍርተዋል፡፡ ያላመኑትንም አሳምነው ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን በመመለስ ለዘላለማዊ ክብር የበቁ እንዲሆኑ አስችለዋቸዋል፡፡ በመሆኑም በክርስቶስ በደሙ የተከፈለውን ወደር የሌለውን ዋጋ ዓለም አምኖና አውቆ በክርስትና ሃይማኖት እንዲድንበትና እዲጠቀምበት በማድረግ እንዲሁም በታማኝነት ሥራቸው ጥንትም ዛሬም ላለችዋና ወደፊትም ለምትኖርዋ ቅድስት ቤተክርስቲያን ድምቀትም ውበትም የሆኑት ቅዱሳን አበው ሊገኙ የቻሉት ከእግዚአብሔር ይልቅ ሰውን ደስ ለማሰኘት በመድከማቸው ሳይሆን የተጠሩበትን ዓላማና የጠራቸውን እርሱን በሚገባ አውቀውና ከልብ ተረድተው ለዘላለማዊ ህይወት ተግተው በመሥራታቸው ነው፡፡ (ገላ1፥10)
ዛሬም በዚህ ዘመን ያለንና በክርስቶስ ክርስቲያን ተብለን የተጠራን ሁላችንም የተሰጠንን መክሊት (ጸጋ) አውቀን ለእግዚአብሔር ለአምላካችን በመታመን ወጥተን ወርደን ሌላ ልናተርፍ ይገባናል፡፡ በተለይ ደግሞ በክህነት አገልግሎት ውስጥ ያለ ሰው ከምንም በላይ በከፍተኛ መንፈሳዊ ኃላፊነት ላይ ያለ እንደመሆኑ መጠን በሃይማኖትም በሥነምግባርም ለሌላው ዓርዓያ በመሆን እንደ እርሱ ሃይማኖትን ከምግባር ጋር አስተባብረው የያዙ ምእመናንን ማፍራት አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ብቻ ነው አንተ በጎ ታማኝ ባሪያ በጥቂቱ ታምነሃልና ወደ ጌታህ ደስታ ግባ ልንባል የምንችለው፡፡ 

አሁን ባለንበት በዘመናችን ብዙ ፈታኝ የሆኑ ችግሮች አሉ፡፡ የችግሮቹም መሠረታዊ ምንጭ በተጠሩበት ጸንቶ መቆም ፈጽሞ አለመቻልና ለሥጋዊ ጥቅም ብቻ በማድላት ኃላፊነትን መዘንጋት ናቸው፡፡ በሥጋዊ አምሮት ፍላጎትና ምርጫ ውስጥ ደግሞ መንፈሳዊ ጸጋንና በረከትን ለማግኘት የሚያስችለንን የታማኝነት ሥራን መሥራት አይቻልምና ከምናድነው ሰው ይልቅ መክሊታችንን በመቅበር መሰናክል የምንሆንበት ሰው ሊበዛ እንደሚችል አያጠራጥርም፡፡ በመሆኑም ከእርሱ ዘንድ እንደዓቅማችን የተሰጠንን መንፈሳዊ ዕውቀት ለሌላው በማድረስ መክሊታችንን ልናበዛ የምንችለውና አገልግሎታችን ወይም ክርስትናችን ውጤታማ የሚሆነው ምርጫችንን አውቀን እንደ ቃሉ ሆነንና ጸንተን ስንገኝ ብቻ ነው፡፡

ይህ ባለመሆኑ ነው ዛሬ ብዙዎቻችን በህይወታችን ሌላውን ማትረፍ አቅቶን በእግዚአብሔርና በሰውም ዘንድ በሚያስወቅሰን የስንፍና መንገድ ላይ ቆመን የምንገኘው፡፡ ስለዚህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ›› (ማቴ24፥42) ብሎናል፡፡
እንግዲህ ቃሉን የሰማንና የምናውቅ ሁላችን በሞቱ ላዳነን፣ በልጅነት ጸጋም ላከበረን፣ በትንሣኤውም ላረጋጋን፣ በመስቀሉ ጥልን ገድሎ ከራሱ ጋር ላስታረቀን፣ በደሙም መፍሰስ ህይወትን፣ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ በረከትንና ዘላለማዊ ደስታን ለሰጠን አምላክ ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በመታመን እርሱ ያዘዘንን ሁሉ ልናደርግ ይገባናል፡፡ ምን ጊዜም ትጉህ ሠራተኛ ደግሞ የሚሠራው መልካም ሥራ ሁሉ ለቤተ ክርስቲያንም ለሀገርም የሚሰጠው ጥቅም እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ በመሆኑም በጎና ታማኝ አገልጋዮች ሆነን እንድንገኝ ጠንክረን ልንሠራ ይገባናል፡፡

የማይቀበሩ መክሊቶች

   በዲ/ን ምትኩ አበራ
 
«ወደ ሌላ አገር የሚሔድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንዲሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና፣ ለእያንዳንዱ እንደአቅሙ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወዲያው ሔደ…» ማቴ 25÷14  ይህንን ታሪክ ማንሣታችን በወርኃ ዐቢይ ጾም በዕለተ ገብርሔር አንድም እየተባለ የሚተነተነውን ቃለ እግዚአብሔር ለማውረድ ተፈልጎ አይደለም፡፡
ጌታችን የተናገራቸው ሁለቱ ኃይለ ቃላት የሚያስደምሙ ስለሆኑ ነው «… እንዲሁ ይሆናልና” የሚለውና «ለእያንዳንዱ እንደአቅሙ» የሚሉት፡፡ ጌታችን እንዳለው እንዲሁ እንዳይሆንብን ዳሩ ግን እንዲሁ እንዲሆንልን ቅዱስ ፈቃዱን እየተማፀን ለእያንዳንዳችን እንደአቅማችን የተሰጡንን የማይቀበሩ መክሊቶች በአጭሩ እንመልከት፡፡
እንደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሥርዓትና እምነታችን እኛ በአርባና በሰማንያ ቀናችን በጥምቀት ከቅድስት ቤተክርስቲያናችን የተወለድን ሁላችን፤ ባለጸጎች/የጸጋ ባለቤቶች፣ ነን « እንደተሰጠን ጸጋ ልዩ ልዩ ሥጦታ አለን» ሮሜ 12÷6 ነገር ግን አንዳንዶች የተሰጠንን ጸጋ ባለማወቅ፣ ሌሎቻችንም የያዝነው ጸጋ ስጦታ ሳይሆን በእኛ ጥበብ ያገኘነው እየመሰለን ወዘተ… እንኳንስ ልናተርፍባቸው ቀርቶ ቀብረናቸው፤ የጸጋውን ባለቤት «አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፡፡ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁና ፈራሁህ፣ ሔጄም መክሊትህን በምድር ቀበርኩት እነሆ መክሊትህ» ለማለት የተዘጋጀን ይመስላል ማቴ 25÷24፡፡
እንድናተርፍባቸው ከተሰጡንና የማይቀበሩ ከሚባሉት መክሊቶቻችን መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
ዕውቀት
ዕውቀት ለፍጡራን ሁሉ የባሕርይ ሳይሆን ተከፍሎ የሚሰጥና የሚነሳ /የሚወሰድ/ ነው፡፡ ይህ ዕውቀት መክሊት/ስጦታ/ ነው፤ 1ቆሮ21÷7 የተሰጠበት ምክንያት ደግሞ እንድንታበይበት ሳይሆን ለሌላው እንድንጠቅምበት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ «ዕውቀት ያስታብያል»  ስለሚል አበው ሲመርቁ ዕውቀት ያለትዕቢት ይስጥህ፤ ይላሉ 1ቆሮ1-3፡፡ ዲያብሎስ አዋቂ ተደርጐ ተፈጥሯልና አዋቂ ነው፡፡ በዚህ ዕውቀቱ ግን እሱ ጠፍቶበት ሌላውን ለማጥፋት ይተጋበታል እንጅ ለሌላው ለመጥቀም አንዳች አይሠራም፡፡ ሰው በተሰጠው ዕውቀቱ በጎ ሥራን እንዲሠራበትና ለሌላው እንዲተርፍበት እግዚአብሔር ይሻል፡፡ እግዚአብሔር የሚጠይቀን በተሰጠን የዕውቀት መክሊት ክፉ ሥራ ስለሠራንበት ብቻ አይደለም በዕውቀታችን መጠን ያላወቀውን ከማሳወቅ ጀምሮ ምን ያህል እንደሠራንበት ይመረምረናል፡፡ ስለዚህ ብዙ ባወቅን ቁጥር ብዙ ማትረፍ እንዳለብን መረዳት ያሻል፡፡ «ብዙ ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል» ተብሏልና፡፡
 ሀብት
በመጀመሪያ ደረጃ ሀብታም/ባለሀብት/ መሆን በክርስትና ሕይወት አይነቀፍም፡፡ ለእግዚአብሔር ፍርድ ምድራዊ ሀብት መመዘኛ አይሆንም፡፡ እሱ ሀብታሙን ፈርቶ ድሃውን ንቆ ሳይሆን ለሁሉም እንደየሥራቸው ነው የሚፈርድባቸው፤ ራዕ 22÷12 ሀብት በምንለው በዚህ ዓለም በንብረትና ገንዘብ በከበርን ጊዜ ሁላችን ልናስታውሰው የሚገባ ቁምነገር አለ፡፡
•  አንደኛ የሰጠን እግዚአብሔር መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ እርግጥ ነው ወጥተን ወርደን ጥረን ግረን ሥራ ሳንመርጥ በላባችን ወዝ ያፈራነው የድካማችን ውጤት ነው፡፡ ግን ይህን ሁሉ ብቻችንን ልናደርገው አንችልም፡፡ በመግባት በመውጣታችን ጊዜ የረዳን፣ ጉልበታችንን ያጠነከረ፣ እጃችንን ያበረታ፣ ጤናውን የሰጠን እግዚአብሔር ነው፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ መጽሐፍ «ጉልበቴ የእጄም ብርታት ይህን ሀብት አመጣልኝ እንዳትል» የሚለን /ዘዳ 8÷17/፡፡
• ሁለተኛው ደግሞ ታማኝ መጋቢ እንድንሆንለት ማለትም ቀን ከፍቶበት ሆድ ብሶት ሲቸገር ያየነውን ወንድማችንን ችግሩን እንድናስወግድለት ላጣውና ለነጣው ድሃ እንድንደርስለት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለመንፈስ ቅዱስ ልጁ ለጢሞቴዎስ «ባለጠጎች ሊረዱና ሊያካፍሉ የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው» ያለው፤ ይህንኑ ለማስታወስ ነው 1ኛ ጢሞ 6÷19 ጠቢቡ ሰሎሞንም ሀብት የማትረፊያ መክሊት መሆኑን ሲያስረዳ «ያለውን የሚበትን ሰው አለ፤ ይጨመርለታልም፤ ያለቅጥ የሚነፍግ ሰውም አለ ይደኸያልም»  ነው ያለው ምሳ 11÷24 ይህ ሰው ለሰዎች ሲሰጥ በምድር ይከፍሉኛል ብሎ አስቦ ባለመሆኑ የሚበትን በማለት በዚህ በሚያልፈው ምድራዊ ሀብት የማያልፈውን ሰማያዊ ሀብት ማትረፍ እንዲቻል የነገረንን ልብ እንበል፡፡ ቀላል ምሳሌ እናስቀምጥ፤ በሰፈራችን አንድ ትልቅ ድግስ ላይ የድግሱ ባለቤት ጐረቤቶቹንና ወዳጆቹን ጠርቶ፤ የድግሱ እድምተኞች ከመምጣታቸው አስቀድሞ፤ አንዱን ወጥቤት፣ ሌላውን ሥጋ ቤት፣ ሌላዋን እንጀራ ቤት ወዘተ እያለ ይመድባል፡፡ እነዚህ ሰዎች የድግስ ቤቱ ሹማምንት ቢሆኑም ድግሱ የእነሱ አይደለም ስለዚህ በሰው ድግስ ለመጠቃቀም አንዱ ባዶ ሳህን ይዞ እያዩ ለሌላው ሁለተኛ እንጀራ ቢደርቡለት፣ አንዱ ደረቅ እንጀራ እየበላ ለሚያውቁት የሰፈራቸው ሰው የወጥ ሳህኑን አቅርበው ወጡን ቢገለብጡለት፣ የሰው ድግስ በማበላሸታቸው ይጠየቁበታል እንጂ አይመሰገኑበትም የዚህ ዓለም ባለጸጐችም እንዲሁ ናቸው የተሰጣቸው ሀብት ሊያጋፍሩበት፣ ሊያስተናብሩበት፣ መክሊት ሊያተርፉበት እንጂ በዚህ ዓለም ሊመራረጡበት በልጠው ሊታዩበት ወዘተ… አይደለም፡፡ « የአመጻ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለም ቤቶች እንዲቀበሏችሁ በእርሱ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ” የተባለውን፤ ባለጸጎች ሁሉ ልብ ሊሉት ይገባል፡፡/ሉቃ 16÷9/
ሥልጣን
ሌላኛው መክሊት ሥልጣን ነው፡፡ ሥልጣን ሲባል ሁሌም ትዝ የሚለን ያየነውም እሱኑ ብቻ ስለሆነ ይመስላል፤ መፍለጥ መቁረጥ፣ ማራድና ማንቀጥቀጥ ነው፡፡ ተረታችንም «ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል» የሚል ነው፡፡ በዚህ መንፈስ ብዙዎች «እኔ እግዚአብሔርን ብሆን ኖሮ…» ብለው የሚፎክሩት አይሆኑም እንጂ ቢሆኑ ኖሮ፤ ከቤተ ክርስቲያን የሚያባርሩት፣ ከሥልጣን የሚሽሩት ወደሞት የሚያወርዱት ባጠቃላይ የሚፈልጡትና የሚቆርጡት ብዙ ነው፡፡ አላወቁትም እንጂ እግዚአብሔርን መሆን እነሱ እንዳሰቡት መቅሰፍ መግደል ብቻ ሳይሆን፤ እግር ማጠብ በጥፊ መመታት፣ በምራቅ መታጠብ፣ የእሾህ አክሊል መድፋት፣ በጦር መወጋት፣ ለሰው ልጆች ድኀነት መሰቀልና መሞትም ነው፡፡  በአንጻሩ በተሰጠው መክሊት ያላተረፈው፤ ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል በሚል አሳብ ተተብትቦ፤ ሥልጣን መፍለጥ መቁረጥ የመሠለው ምስኪን የሚያገኘውን ዕድል በምሳሌ ሲያስረዳ እንዲህ ብሏል፡፡ «ያባሪያ ግን ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል ብሎ በልቡ ቢያስብ ሎሌዎችንና ገረዶችንም ይመታ፣ ይበላም ይጠጣም ይሰክርም ዘንድ ቢጀምር የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቃት ሰዓት ይመጣል ከሁለትም ይሰነጥቀዋል ዕድሉንም ከማይታመኑ ጋር ያደርጋል፡፡» /ሉቃ 12÷42-46/፡፡ ጥሩ ክርስቲያን ባለሥልጣን ሲሆን አይኮፈስም፤ «ጌታው በቤተሰቦቹ ላይ የሾመው፡፡» ተብሎ እንደተጠቀሰው፤ በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ በመሾሙ እንደጠቢቡ ሰሎሞን ይህንን ሕዝብ የማስተዳድርበት ጥበብ ስጠኝ እያለ ወደ ፊጣሪው በመጸለይ መክሊቱን ለማትረፍ ይተጋል፡፡
አንድ ታሪክ እናስታውሳችሁ፤ የሊቀ ጳጳሱ የዲሜጥሮስን ወደ ጵጵስና መዓርግ መምጣት እናቱ ሰምታ «ሹ

“መከራ ልትቀበሉ እንጂ በስሙ ልታምኑ ብቻ አልተጠራችሁም” (ፊል. ፩፥፳፱)



ዘመናችን መረጃ በፍጥነት የሚለዋወጥበት፣ ስላሙ ሲደፈርስ ደቂቃ የማይፈጅበት እየሆነ መጥቷል፡፡ ሰዎች ሞትን ለመሸሽ የማያደርጉት ጥረት የለም፡፡ ኃያላን ሰማይ ጠቀስ ፎቆች፣ የኤሌክትሪክ አጥር፣ የድኅንነት ካሜራ እያዘጋጁ ወንጀልንና ወንጀለኞችን ለመቆጣጠር ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም፡፡ መንገዳቸው ሥጋዊ ፍላጎትን የተከተለ በመሆኑ መፍትሔ ማሰገኘት አልቻለም፡፡ ችግሩ የሚፈታው ሁልጊዜ ችግርን ወደ ሌላ በመጠቆም አለመሆኑን መረዳት ይገባል፡፡
ምዕራባውያን የአዳጊ ሀገሮችን ቅርስና መዋዕለ ንዋይ እየዘረፉ ወደ ሀገራቸው ሲወሰዱ ኖረዋል፡፡ አሁን ደግሞ እነሱው ባሳዩዋቸው መንገድ ሌሎች ሀብታሞች የሰበሰቡትን እንዳይበሉት እያደረጉዋቸው ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ሒደት ከምኑም የሌሉበት ክርስቲያኖች ለአደጋ እየተጋለጡ፣ የሚደርስላቸው አጥተው እግዚአብሔርን እየተማጠኑ ነው፡፡ ለዚህ አብነት የሚሆኑን የሶሪያ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ የተሸፈነው ሁሉ የእልክ መወጫና የጦር መለማመጃ የሚያደርገው ክርስቲያኖችን ነው፡፡ መስቀል የጨበጡ ካህናትን ገድሎ የሚገኝ ደስታ፣ ምእመናንን የሚያረጋጋና ለሀገር ሰላም የሚጸልይን ጳጳስ አስሮ የሚገኝ ሰላም እንዴት ያለ ሰላም ሊሆን እንደሚችል መገመት ያዳግታል፡፡
በመካከላችን የተፈጠረውን ልዩነት ተወያይተን እንፍታው፣ ከጦርነት ጥፋት እንጂ ልማት አናገኝም የሚሉት ወገኖች እየቀነሱ መጥተዋል፡፡ ሀገር በወንበዴዎች ጠፍታ እንደምታድር በሰላማውያን ደግሞ ተሠርታ ታድራለች፡፡ ሰላማውያን ከሆንን ለእኛ የሚያስፈልገን ለሌሎችም እንደሚያስፈልጋቸው ስለምናምን ያለውን ተካፍለን እንጠቀማለን፣ ከሌለ ደግሞ በጋራ ሠርተን የምናገኝበትን ዘዴ እንቀይሳለን፡፡ በዓለማችን እየተሠራ ያለው ግን የሌላውን ነጥቆ የራስ ማድረግ ነው፡፡ የድሀ ሀገሮችን ቅርስ፣ ንዋያተ ቅድሳት እየዘረፉ ወስደው የራሳቸው የሚመስልበትን ሕግ አውጥተው ይኖራሉ፡፡ የታሪኩ ባለቤቶች የራሳቸውን ንዋያተ ቅድሳት ከፍለው ይመለከታሉ፡፡ ይህም የዓለም ሕግጋት የተንሸዋረረና ላለው የሚያደላ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ ትክክለኛ መፍትሔ ለማምጣት ከተፈለገ ፍትሕ ያለ አድሎ ለሁሉም መስጠትና በኢኮኖሚ የዳበሩት ሀገሮች ድሆችን እናውቅላችኋለን፣ እኛ ያልናችሁን ብቻ ፈጽሙ የሚለው አሠራር መታረም አለበት፡፡
እምነት ያላቸው ሰዎች ግን እንኳን የሌላውን ሊነጥቁ የራሳቸውንም አሳልፈው ይሰጣሉ፡፡ መመሪያቸውም “እምነትስ ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የምታስረግጥ፣ የማናየውንም ነገር የምታስረዳ ናት፡፡ በዚህም ለሸማግሌዎች ተመሰከረላቸው፡፡ ዓለም በእግዚአብሔር ቃል እንደተፈጠረ፣ የሚታየውም ነገር ከማይታየው እንደሆነ በእምነት እናውቃለን” (ዕብ. ፲፩፥፲፫) የሚለው ቃል ነው፡፡ ተስፋቸው ለዘለዓለማዊው ዓለም በመሆኑም በምድር ሰላማውያን ሆነው ይኖራሉ፡፡ የማይታየውን ተስፋ ስለሚያደርጉም እንደሚታረድ በግ እየተጎተቱ ወደ ሞት ሲወሰዱ በደስታ ይቀበሉታል፡፡ ሞትንም የሚንቁት ከመከራ፣ ከውጣውረድ፣ ከስቃይ የሚያርፉበትና ዳግም ሞት ወደሌለበት የሚሸጋገሩበት በመሆኑ ነው፡፡
ክርስቲያኖች በዚህ ምድር ሲኖሩ ደስታና ኀዘን፣ ማግኘትና ማጣት ቢፈራረቅባቸውም ታግለው ለማሸነፍ፣ እግዚአብሔርን ጠይቀውም መፍትሔ ለማምጣ ይሞክራሉ፡፡ የሚደርስባቸውን ፈተና በጸጋ የሚቀበሉትም በተስፋ ኗሪዎች ሀገራቸው በሰማይ መሆኑን በደንብ የተረዱ በመሆናቸው ነው፡፡ ኃይል እያላቸው የሚሸሹት፣ ማድረግ እየቻሉ አቅም የሌላቸው የሚመስሉት ዘለዓለማዊው ድኅነት በመሞት እንጂ በመግደል የሚገኝ ባለመሆኑ በመስጠት እንጂ በመቀማት ባለመገኘቱ ነው፡፡ የነገሥታት ወገኖች የነበሩት ሰማዕቱ ቅዱስ አቦሊ፣ አባቱ ዮስጦስና እናቱ ታውክልያ ዙፋኑ ለእነሱ እንደሚገባ እያወቁ ስለዘለዓለማዊው ጊዜያውን ናቁት፡፡ የሮማ ሕዝብ ከዲዮቅልጥያኖስ እነሱ እንደሚሻሉት፣ በጉልበት ሳይሆን በእምነት እንደሚመሩት እነሱም፣ ዲዮቅልጥያስም፣ ሕዝቡም ያውቃሉ፡፡ ያደረጉት ግን ለክርስትና ፍቅር ብለው ሥልጣናቸውን መተውና ሰማዕትነትን መቀበል ነው፡፡ አቅም የላቸውም እንዳይባሉ ብቻቸውን ተዋግተው የጠላት ሠራዊት መመለስ እንደሚችሉ አሳይተዋል፡፡ ክርስትናቸው ግን ከዚያ እንዲያልፉ አላደረጋቸውም፡፡ በዚህም ገዳያቸው ዲዮቅልጥያኖስ በክፉ እነሱ ግን በመልካም ሲታወሱ እንዲኖሩ የሚያደርጋቸውን ሥራ ሠርተው ዐልፈዋል፡፡ ሁልጊዜ አስቡን፣ ከአምላካችሁ አስታርቁን እየተባሉ ይለመናሉ፡፡
ክርስቲያኖች እምነት እንጂ ፍርሃት መገለጫቸው አይደለም፡፡ ጦር መሣሪያ የታጠቁት ባዶዋቸውን የቆሙትን ክርስቲያኖች የሚፈሯቸው እምነት ያላቸው ሰዎች እግዚአብሔር አብሯቸው ስለአለ ምን ያህል እንደሚያስፈሩ ማሳያ ነው፡፡ መፍራት የነበረበት ባዶ እጁን ያለና ሞት የተፈረደበት እንጂ ንጹሐንን ወደ ሞት በመውሰድ የሚገድል አይደለም፡፡ በክርስቲያኖች የሚፈጸመው ግን የተገላቢጦሽ ነው፡፡ ንጉሡ እለእስክንድሮስ በፍርሃት እንዲርድ ያደረገው የሦስት ዓመቱ ሰማዕቱ ቂርቆስ ነው፡፡ የእምነት ሰዎችን አላውያን ነገሥታት ብቻ ሳይሆኑ አጋንንትም ይፈሯቸዋል፡፡
እምነታቸውን ጋሻ በማድረጋቸው ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን በአጸደ ሥጋ ለምንኖር ሁሉ ኃይላችን፣ ብርታታችን፣ ትውክልታችን፣ ጋሻ መከታችን መሆናቸውን ሐዋርያው “እነሱ በእምነት ተጋደሉ፤ ነገሥታትን ድል ነሡ፤ ጽድቅን አደረጉ፣ ተስፋቸውን አገኙ፣ የአናብስትን አፍ ዘጉ፡፡ የእሳትን ኃይል አጠፉ፤ ከሰይፉ ስለት አመለጡ፤ ከድካማቸው በረቱ፣ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፤ የባዕድ ጭፍሮችንም አባረሩ፡፡ ሴቶችም እንደ ትንሣኤ ቀን፣ ተነሥተውላቸው ሙታኖቻቸውን ተቀበሉ፤ ተፈርዶባቸው የሞቱም አሉ፤… የገረፉዋቸው፣ የዘበቱባቸውና ያሰሩዋቸው ወደ ወኅኒ ያስገቧቸው አሉ፡፡ በመጋዝ የሰነጠቋቸው፣ በድንጋይ የወገሯቸው፣ በሰይፍም ስለት የገደሏቸው አሉ፤ ማቅ፣ ምንጣና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ተጨነቁ፣ ተቸገሩ፣ መከራ ተቀበሉ፣ ተራቡ፣ ተጠሙም፡፡ ዓለም የማይገባቸው እነዚህ ናቸው፤ ዱር ለዱርና ተራራ ለተራራ፣ ዋሻ ለዋሻና ፍርኩታ ለፍርኩታም ዞሩ (ዕብ. ፲፩፥፴፫-፴፰) በማለት ገለጠው፡፡ የእስራኤል ኃያላን የሃይማኖት ሰዎች ሕዝበ እግዚአብሔርን ለመጠበቅ ያደረጉትን ተጋድሎ በመዘርዘር ወደ ሐዲስ ኪዳን ሰማዕታት የሚሸጋገረው የሐዋርያው ትምህርት ለደከሙት ብርታት የሚሆን ነው፡፡
ሐዋርያው አስቀድሞ እምነታቸውን ነገረን፡፡ በመቀጠልም እምነታቸውን ለመጠበቅ የፈጸሙትን ተጋድሎ አስረዳን፡፡ አስከትሎም በዚህ ዓለም በፈጸሙት ተጋድሎ በእምነት እንደተመሰከረላቸው፣ የተስፋ ቃል እንደተገባላቸው አበሰረን፡፡ ሐዋርያው የእነዚህን አበው ተጋድሎ የተረከልን በእምነት እንድንጸና፣ በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ፈተና ዛሬ አለመጀመሩን ተገንዝበን እንድንረዳው ነው፡፡ ወታደር ጀብድ የፈጸሙ ጀግኖችን ተጋድሎ እየተረከ የወታደሮችን ስሜት እንደሚቀሰቅስና ፍርሃታቸውን እንደሚያርቅላቸው ሁሉ ክርስቲያኖችም በእምነት የጸኑትን፣ ይህን ዓለም ታግለው ያሸንፉትን መንፈሳዊ ተጋድሎ በመተረክ አርአያ እንድናደርጋቸው እናንተን ያጸና እኛንም ያጽናን እንድንላቸው ነው፡፡ በሃይማኖት ጽኑ፣ የሚያልፈውን በማያልፈው ለመተካት የሚደርስባችሁን ታገሱ፣ በእምነት ጽኑ፣ ጎልምሱም የሚለው ትምህርት ለክርስቲያኖች ስንቅ ነው፡፡ ፍርሃትን አርቆ በእምነት ለመጽናት የሚያበቃ ነው፡፡
በተስፋ የሚጠብቁት ስለበለጠባቸው በዚህ ዓለም የሚደርስባቸውን መከራ መታገሥ እንዳለባቸው ሐዋርያው “እኔስ ከዚህ ዓለም ልለይ በክርስቶስም ዘንድ ልኖር እወዳለሁ፡፡ ይልቁንም ለእኔ ይህ ይሻለኛልና፤ ይበልጥብኛል፡፡ ደግሞም ስለ እናንተ በሕይወተ ሥጋ ብኖር ይሻላል፡፡ ይህንም ዐውቄ ለማደጋችሁና ለሃይማኖትም ለምታገኙት ደስታ እንደምኖር አምናለሁ” (ፊል. ፩፥፳፫-፳፭) በማለት ገልጦታል፡፡ በዚህ ቃል ሐዋርያው የራሱን ፍላጎት ገለጠ፡፡ ለምእመናንና ለቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልገውንም አሳወቀ፡፡ የሃይማኖት ሰዎች እንደነሱ ፈቃድ ብቻ ሳይሆን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መኖር እንደሚገባ አስገነዘበ፡፡ ይህም ክርስቲያኖች ሌላውን ለመጥቀም ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር ቢናፍቁ እንኳ ሊያዘገዩት እንደሚችሉ ያስረዳል፡፡
ቤተ ክርስቲያን ትገፋለች፡፡ ወድቃ ግን አታውቅም፡፡ የሚገርመው አላውያን ቤተ ክርስቲያንን ለመግፋት የዘረጉት እጃቸው እምነትን ገንዘብ አድርጎ መመለሱን እያየን መሆኑ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ጉዞ እንዲህ ነው፡፡ አንዱ ሲቆረጥ ከሥሩ በሺሕ የሚቆጠሩ እያበቀለ ክርስትና እንድታብብ አድርጓል፡፡ የሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የዘመነ ሰማዕታት ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆኑ በሀገራችንም ሰማዕትነት አያምልጥህ እያሉ በአንድ ቀን ስምንት ሺሕ ገበሬ ምእመናን ሰማዕታትን ተቀብለዋል፡፡ ይህም በታሪክ እንዲዘከሩ፣ በቤተ ክርስቲያን እንዲታሰቡ አድርጓቸው ይኖራል፡፡
በየዘመኑ ዲያብሎስ በቤተ ክርስቲያን ላይ ፈተና ያስነሣል፡፡ አይታለፍም የተባለው ታልፎ፣ አይሆንም የተባለው ተፈጽሞ እየታየ ነው፡፡ ለዚህም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “ዲያብሎስ ዝናሩን አራገፈ፤ ቀስቱን ጨረሰ፤ ቤተ ክርስቲያንን ግን አልጎዳትም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜ ትዋጋለች፤ ተሸንፋ ግን አታውቅም” በማለት መናገሩ ምስክር ነው፡፡ ዲያብሎስ እንደማያሸንፉት እያወቀ፣ ክርስቲያኖችም በጸሎት ኃይል እንደሚያደክሙ እየተረዳ ቤተ ክርስቲያንን ይዋጋል፡፡ ዲያብሎስ የሚያተርፈው ቢኖር ቤተ ክርስቲያንን ለመዋጋት ያሰለፋቸው ጀሌዎቹ በክፋታቸው ከጸኑለት አብረውት ገሃነመ እሳት እንዲወርዱ ማድረግ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ የአባቶቻችንና እናቶቻችን ቅድስና እንዲገለጥ ያደርጋል እንጂ ያሰበው ተሳክቶለት፣ ምኞቱ ሞልቶለት አያውቅም፡፡
ክርስቲያኖች ክርስትናን የተቀበሉት፣ የሥላሴ ልጅነትን ያገኙት ለማመን ብቻ ሳይሆን መከራም ለመቀበል መሆኑን ሐዋርያው “የእነሱ ጥፋት የእናንተም ሕይወት ይታወቅ ዘንድ የሚቃወሙትን ሰዎች በማናቸውም አያስደንግጧችሁ፡፡ ይህንም ጸጋ እግዚአብሔር ሰጥቷችኋል፤ ነገር ግን ስለ እርሱ መከራ ልትቀበሉም ነው እንጂ ልታምኑበት ብቻ አይደለም፡፡ እንዲሁም እኔን እንዳያችሁኝ የእኔንም ነገር እንደሰማችሁ ምን ጊዜም ተጋደሉ” (ፊል. ፩፥፳፰-፴) በማለት ገልጦልናል፡፡ ይህን የምንለው ክርስቲያኖች በዚህ ዓለም ሲኖር መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ምንም አያስፈልጋቸውም ለማለት አይደለም፡፡ ከሁሉ የሚቀድመው በእምነት ጸንቶ፣ ነቅቶና ተዘጋጅቶ መኖር እንደሚያስፈልግ ለመግለጥ እንጂ፡፡ እምነት ያላቸውና ትውክልታቸውን በእግዚአብሔር ላይ ያደረጉ ደግሞ በዚህ ዓለም እንዴት እንደሚኖሩ ያውቁነታል፡፡ ራሳቸው ዘመኑን ዋጅተው ነው እኛንም ዘመኑን ዋጁ የሚሉን፡፡
የክርስትና ማእበል በሆነችው ኢትዮጵያ የዘር፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የባህል ልዩነት ሳይገድበን ተንቀሳቅሰን ይመቸናል በምንለው አካባቢ ወልደን፣ ከብደን፣ ወጥተን፣ ወርደን፣ ነግደን አትርፈን እንኖራለን፡፡ ማን ነህ፣ ከየት መጣህ፣ ሃይማኖትህ ምንድን ነው የሚል ወገን በሀገራችን አይታሰብም ነበር፡፡ ዓለምን ከምናስደንቅበት ነገር አንዱ በሌሎች ዓለማት በበጎ የማይታዩት ክርስትናና እስልምና በኢትዮጵያ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ሆነው መኖራቸው ነው፡፡ በብዙዎች አካባቢዎች ክርስቲያኖች ቤተ ክርስቲያን መሥሪያ ሲያጡ ከመሬታቸው ቆርሰው፣ ከኪሳቸው ገንዘብ አውጥተው፣ የሰበካ ጉባኤ አባል ሆነው አብያተ ክርስቲያናትን ያሠሩ ብዙ ሙስሊም ወገኖቻችን ነበሩ፤ አሁንም አሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያን ዕቃ ቤት ጠባቂ የሆኑና ቤተ ክርስቲያንን በጥበቃነት የሚያገለግሉ ሙስሊም ወገኖቻችን መኖራቸው የሚገልጠው በሃይማኖት ልዩ ብንሆን በማኅበራዊ ሕይወት፣ በባህል ለምን እንለያለን ብለው ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ታሪኮችን በሐመር መጽሔት፣ በስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ፣ በማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ስርጭት ስናስተላልፍ መቆየታችን ይታወቃል፡፡ ይህንን የምንገልጠው ለፕሮፓጋንዳ ሳይሆን በትክክል የተፈጸመ መሆኑን ለመግለጥ ነው፡፡ የገረመንም እንዲህ በሚደረግባት ሀገር ቤተ ክርስቲያንና ክርስቲያኖች የጥፋት ዓላማ እየሆኑ በመምጣቸው ነው፡፡
ሰሞኑን በሶማሌ ክልል ክርስቲያኖችን ብቻና ቤተ ክርስቲያንን መርጠው ጥፋት ሲታወጅባቸው የእስልምና ጉዳዮችም፣ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንም ድርጊቱን እንደሚያወግዙት የገለጡት የአንዱ በሰላም ማደር ለራስ ሰላምም ስለሚጠቅም ነው፡፡ በሌላ በኩልም እንዲህ ያለ ጥፋት በሀገራችን ያልተለመደ መሆኑን ስለሚያውቁ ነው፡፡ ልዩ ልዩ ወገኖች የሰጡት መግለጫ እንዲያውም ቤተ ክርስቲያኗ ከሰጠችው የጠነከረ ነው፡፡ አሜሪካና ኢትዮጵያ ይኖሩ የነበሩ አባቶች ይቅር ተባብለው ዕርቁንም በሚሊኒየም አዳራሽ ባበሠሩበት ወቅት የእስልምና፣ የካቶሊክ፣ የወንጌላውያን ኅብረትና የቃለ ሕይወት ተወካዮች ያደረጉት ንግግር ይህ ድምፅ ከቤተ ክርስቲያን ነው ከሌላ የሚያሰኝ ነበር፡፡ ይህ ደስታ ሳይፈጸም በክርስቲያኖችና በቤተ ክርስቲያን ላይ ጭፍጨፋና ቃጠሎ ተተካ፡፡ ሕግና ሥርዓት ባለበት ሀገር እንዲህ ማድረግ ተገቢ አለመሆኑን የምንገልጠው ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ በተሳለ ሰይፍ ላይ ለቆሙት በማዘን ነው፡፡ አስቀድመን እንደተናገርነው ቤተ ክርስቲያንን ብዙዎች ለመግፋት ሞክረው ነበር አልቻሉም እንጂ፡፡ ዐርፍተ ዘመን ገትቷቸው፣ ተአምር ተደርጎ ተመልሰው አምላኬ ሆይ ሳላውቅ ባጠፋሁት አትቅሰፈኝ ሲሉ ኖረዋል፡፡ አንመለስም ያሉትም አሟሟታቸው ምን ይመስል እንደነበር የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ ማንበብ በዲዮቅልጥያኖስ፣ የዮልዮስቂሳርና በሌሎችም የደረሰውን ማሰብ ይገባል፡፡
የሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስን ቤተ ክርስቲያን ለማፍረስ ሞክሮ የነበረው ዲዮቅልጥዮስ የደረሰበትን መከራ ገድሉንና ስንክሳር መጽሐፉን ማንበብ ይገባል፡፡ በቅድስት አርሴማና በተከታዮቿ ላይ በቃላት ተነግሮ የማያልቅ መከራ አድርሶ የነበረው የአርማንያው ንጉሥ ድርጣድስ አእምሮው ተነሥቶት ለሰባት ዓመታት እንደ በራሃ እሪያ ሣር ሲበላ ኖሮ በገባሬ ተአምራት ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘአርማንያ ጸሎት እንደዳነ፣ ታላቁ ባስልዮስ ዘቂሳርያንና ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙን ከዋሉበት አላሳድር፣ ካደሩበት አላውል ብሎ የነበረው በአቴንስ የፍልስፍና ትምህርት ቤት የትምህርት ቤት ጓደኛቸው የነበረው ዩልዮስቄሳር መጨረሻቸው አላማረም፡፡ እነሱ ስለ ጓደኝነት፣ ስለ ክርስቶስ ፍቅር ጭምር ብለው ቢታገሱት አልሰማም በማለቱና ከጦርነት ሲመለስ እነሱንም ለመግደል ቤተ ክርስቲያናቸውንም ለማቃጠል ዝቶ ጠላቶቹን ለመውጋት ሲሔድ ቅዱስ ባስልዮስ ክርስቲያኖችን ካሳደደ ከሔደበት በሰላም እንደማይመለስ ነገረው፡፡ ንጉሡ ድንኳን ውስጥ በተኛበት የቅዱስ መርቆርዮስ ሥዕል በጦር ወጋው፡፡ ከአልጋው ሳይነሣ ቀረ፡፡ አጃቢዎቹ ወዳለበት ቢገቡ በደም ተንክሮ ስላገኙት ደንግጠው ተበተኑ፡፡
በክርስቲያኖች ደም እጃቸውን የታጠቡ ወገኖች የደረሰባቸውን ለማወቅ መጻሕፍትን ማንበብ ሊቃውንትን መጠየቅ ይገባል፡፡ እነዚህ ሁሉ ግፈኞች “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” (ማቴ. ፭፥፲፮) ለተባለላቸው ከስቃይ ወደ ረፍት መሸጋገሪያ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የእነሱን ደካማ ጎን የክርስቲያኖችን ጥብዓት የሚገልጥ ነው፡፡ ክርስቲያኖች “ክርስትና ሊኖሩት እንጂ ሊያወሩት ብቻ እንደማይገባ፣ ወንጌል በተግባር ሲገለጥ እንጂ እንደ ርዕዮተ ዓለም በቃላት ብቻ በንግግር ማሳመር እንደማይሰበክ ሕያው ምስክር ናቸው፡፡ ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምን ከመንጸፈዳይን ለማውጣት መከራ ተቀብሏል፤ ሞትንም ድል አድርጎ ተነሥቷል፡፡ ትንሣኤውን በሚመስል ተንሣኤ ተነሥተን ከክርስቶስ ጋር እንኖር ዘንድ ሞቱን በሚመስል ሞት መተባበር እንዳለብን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አስተምሮናል፡፡ የኑሮዋቸውን ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሏቸው የተባልናቸው ዋኖቻችን ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በሁሉ መስለውታል፡፡ እኛም እነሱን እንድንከተልና እንድመስላቸው አርአያነታቸውን መከተል ይገባናል፡፡”
ለእግዚአብሔር ሕዝብ ብሎ መከራ የመቀበልን አርአያነት ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እንድንማር ሐዋርያው “ሙሴ ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኩር ብሎ ተመልክቷልና፡፡… የማይታየውን እንደሚታየው አድርጎ ጸንቶአልና” (ዕብ. ፲፩፥፳፭-፳፯) በማለት አስተምሮናል፡፡ ይህ ሁሉ የሚያስገነዝበው የክርቲያኖች በመከራ የማይገበሩ መሆን ነው፡፡
እንደ ሀገር የምንበለጽገውና ሰላማችን እውን የሚሆነው በሰላም ተከባብረን ስንኖር ነው፡፡ ሰላም ከሌለ ያለንን መጠቀም፣ የጎረስነውን መዋጥ አንችልም፡፡ ሌት ዕንቅልፍ ቀን ረፍት አናገኝም፡፡ ዛሬ በክርስቲያኖችና በቤተ ክርስቲያን ላይ የተጀመረው ጥፋት መልኩን ለውጦ ብዙዎችን እንዳይበላና መጨረሻችንን ዳር ቆመው አይተው መሬታችንን ለመውረር ለሚጎመጁት ጠላቶቻችን መንገድ ጠራጊ እንዳንሆን መጠንቀቅ ይገባናል፡፡ ጥፋት ቢከሠት እንኳ ጥፋትን በጥፋት መመለስ ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም፡፡ የተጠቃሉት አብያተ ክርስቲያናትና የሞቱና የተሰደዱ ክርስቲያኖች እስከ አሁን በክልሉ መንግሥት መልካም ፈቃድና በሕዝቡ አብሮ የመኖር ባህል በቦታው  ብዙ ዓመታት ኖረዋል፡፡ መቀጠል የሚኖርበት እንደ እስከአሁኑ በፍቅር መኖር ነው፡፡ የሚስተካከል ካለ ማስተካከል፣ ጎደሎ ካለ መሙላት፣ የሚያስቸግር ካለ ማስተካከል እንጂ ሰላማውያንን ማወክ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል እንኳን አእምሮ ያለው ሕፃናትም ያውቁታል፡፡ መንግሥት አልባ ለመሆን ካልፈለግንና ሀገራችን ውስጥ ቀምቶ የሚበላ እንዲኖር ካልፈለግን በቀር፡፡ ወደፊት አብረን እንድንኖር የሚያደርጉንን እየተመካከርን መሥራት፣ የሚያስቸግሩ ካሉ ማስተካከል ይገባል፡፡ እምነትን ሽፋን አድርጎ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያለያይ ካለ ቢቻል መክሮ ማስተካከል አልመለስም ካለ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል እያሳወቅን ሰላማችንን ጠብቀን መኖር ይጠበቅብናል፡፡
የተሰደዱት እንዲመለሱ፣ የተቃጠሉት አብያተ ክርስቲያናት እንዲሠሩ፣ የሟች ወገኖች እንዲደገፉ ማድረግ ይገባል፡፡ ችግሩን ወደ ሌላ መጠቆም አይጠቅምም፡፡ የሚጠቅመው መፍትሔ ማበጀትና ፍቅርንና አብሮ መኖርን የሚያጸና ተግባር መፈጸም ነው፡፡ ዐይን ስለ ዐይን የሚለው ሕግ ቀኝህን በመታህ ግራውን አዙርለት በሚለው ቢተካም ለሀገር ደኅንነት ሲባል ጥፋተኞች የሚታረሙበትን፣ ዳግም ለጥፋት እንዳይሰለፉ የሚሆኑበትን ሥራ መሥራት ከመንግሥት፣ ከቤተ ክርስቲያን፣ ከፍትሕ አካላትና ከሚመለከታቸው ሁሉ ይጠበቃል፡፡ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያንና በክርስቲያኖች ላይ የደረሰው “መከራ ልትቀበሉ እንጂ በስሙ ልታምኑ ብቻ አልተጠራችሁም” በማለት ሐዋርያው የተናገረውን እንዳንረሳው ለማድረግ እንደሆነስ ማን ያውቃል፡፡ ማን ያውቃል ነገ ከነገወዲያ ከተቃጠሉት ዐሥር አብያተ ክርስቲያናት ሁለትና ሦስት ዕጥፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚያንፁ ክርስቲያኖችን እግዚአብሔር ሊያሥነሣም እንደሚችል ማመን ያስፈልጋል፡፡
  ምንጭ  ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ከነሐሴ16-ጳጉሜ5ቀን 2010ዓ.ም

ክብረ በዓላት በመጽሐፍ ቅዱስ

 

timket 
በዲያቆን ዘአማኑኤል አንተነህ
የካቲት ፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
በዓል ማለት ‹‹አብዐለ – አከበረ›› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጕሙም ‹‹መታሰቢያ ማድረግ፣ ማክበር›› ማለት ነው፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም በመዝገበ ቃላታቸው ‹‹በዓል (ላት) በቁሙ፣ የደስታ፣ የዕረፍት ቀን፤ በዓመት፣ በወር፣ በሳምንት የሚከበር፤ ያለፈ ነገር የሚታሰብበት፤ ሕዝብ የበዓሉን ምሥጢር እያሰበ ደስ ብሎት እና ለብሶ፣ አጊጦ የሚዘፍንበት የሚዘምርበት፤ ዕልል የሚልበት፤ ሽብሸባ፣ ጭብጨባ የሚያደርግበት፤ ሲያረግድ እስክስታ ሲወርድ ባንገቱ የሚቀጭበት እንደ ጥጃ የሚፈነጭበት ነው›› በማለት የበዓልን ትርጕም ገልጸውታል፡፡ በአጠቃላይ በዓል ማለት ማሰብ፣ መዘከር፣ ማስታወስ የሚል ትርጕም አለው፡፡
የበዓላት ዑደት
እግዚአብሔር አምላካችን ‹‹ይህም ቀን መታሰቢያ ይኹናችሁ፤ ለእግዚአብሔርም በዓል ታደርጉታላችሁ፡፡ ለልጅ ልጃችሁ ሥርዓት ኾኖ ለዘለዓለም ታደርጉታላችሁ፤›› በማለት በዓል ዘለዓለማዊ መታሰቢያ እንደ ኾነ ተናግሯል /ዘፀ.፲፪፥፲፬-፲፯፤ ዘሌ.፳፫፥፪-፬/፡፡ ስለዚህም በዓላት በዓመታት፣ በወራት እና በሳምንታት ዑደት እየተመላለሱ ይከበራሉ፡፡ በየዓመቱ ከምናከብራቸው መንፈሳውያን በዓላት መካከል በዓለ ልደት፣ በዓለ ጥምቀት፣ በዓለ ትንሣኤ ይጠቀሳሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ የልደት በዓልን የምታከብረው ክርስቶስ በየዓመቱ የሚወለድ ኾኖ አይደለም፤ የልደቱን መታሰቢያ ለማሰብ ነው እንጂ፡፡ ጥምቀትን ስታከብርም የወንጌልን አስተምህሮ ተከትላ፣ ምሥጢር አስተካክላ፣ ወቅቱን ‹‹ዘመነ አስተርእዮ›› ብላ ሰይማ የክርስቶስን መገለጥ በማስተማር በዓሉን ታስበዋለች፡፡ የጥምቀት በዓልን እኛ ምእመናን ስናከብርም ዅልጊዜ እንጠመቃለን ማለት አይደለም፤ በዓሉን የምናከብረው ክርስቶስ መጠመቁን ለመዘከር፤ ከበረከቱም ለመሳተፍ ነው፡፡ በዓለ ትንሣኤን የምናከብረውም የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ በማሰብ፣ የእኛንም ትንሣኤ ተስፋ በማድረግ ነው እንጂ ጌታችን በየዓመቱ ከሙታን ይነሣል በማለት አይደለም፡፡ ሌሎችን በዓላትም እንደዚሁ፡፡
በዓላትን በማክበራችን ምን ጥቅም እናገኛለን?
፩. በረከት
‹‹አምላክህ እግዚአብሔር በፍሬህ ዅሉ በእጅህም ሥራ ዅሉ ይባርክሃልና እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ሰባት ቀን በዓል ታደርጋለህ፤ አንተም ፈጽሞ ደስ ይልሃል፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ /ዘዳ.፲፮፥፲፭/ በዓል ማክበር በረከትን ያሰጣል፡፡
፪. ፍጹም ደስታ
በዓል ስናከብር መንፈሳዊ ደስታ ይሰማናል፡፡ በበዓላት ወቅት እርስበርስ በመጠራራት ቤተሰብ ከሩቅም ከቅርብም ይሰባሰባል፤ ዕለቱ የደስታ ቀን ነውና፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴም ‹‹አንተም፣ ወንድ ልጅህና ሴት ልጅህ፣ ወንድ ባሪያህ እና ሴት ባሪያህ፣ በአገርህም ደጅ ውስጥ ያለ ሌዋዊ እና መጻተኛ፣ ድሃ አደግ እና መበለትም በበዓል ደስ ይበላችሁ፤›› በማለት በበዓል ቀን በዓሉን በማክበር መደሰት እንደሚገባ ይናገራል /ዘዳ.፲፮፥፲፬/፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊትም በመዝሙሩ ‹‹በዓል የሚያደርጉ ሰዎች የደስታ እና የምስጋና ቃል አሰሙ፤›› ይላል /መዝ.፵፪፥፬/፡፡ ነቢዩ ዕዝራ ደግሞ ‹‹እግዚአብሔር ደስ አሰኝቷቸዋልና የቂጣውን በዓል ሰባት ቀን በደስታ አደረጉ፤›› ሲል የእስራኤላውያንን በበዓል ቀን መደሰት አስረድቶናል /ዕዝ.፮፥፳፪፤ ፪ኛ ዜና መዋዕል ፴፥፳፫-፳፭/፡፡ በአገራችን አባባልም ‹‹አብሮ የበላን ቅዱስ ዮሐንስ አይሽረውም›› እንደሚባለው በዓመት በዓል ሕዝበ ክርስቲያኑ እርስበርስ እየተጠራራ አብሮ በመብላት በመጠጣት ይጫወታል፤ ይደሰታል፡፡
የበዓላት ክብር እኩል ነውን?
በዓላት በክብር ይለያያሉ፤ ለምሳሌ የእመቤታችን በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየወሩ በ፳፩ ቀን ይከበራል፡፡ መስከረም ፳፩፣ ኅዳር ፳፩፣ እና ጥር ፳፩ ቀን ደግሞ የእመቤታችን ዐበይት በዓላት ናቸው፡፡ እንደዚሁም የቅዱስ ሚካኤል በዓል ወር በገባ በ፲፪ኛው ቀን ይከበራል፡፡ ኾኖም ግን የቅዱስ ሚካኤል ዐቢይ በዓል የሚከበረው በየዓመቱ በኅዳር ፲፪ እና ሰኔ ፲፪ ቀን ነው፡፡ የቅዱስ ገብርኤል ደግሞ በየወሩ በ፲፱ ቀን በዓሉ ቢታሰብም ታኅሣሥ እና ሐምሌ ፲፱ ቀን ዐቢይ በዓሉ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በወር ውስጥ የሚገኙትን እያንዳንዱን ቀናት በቅዱሳን ስም ብትሰይምም በዓላትን በዐቢይነትና ታቦታትን በማውጣት የምታከብራቸው በዓመት አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ነው፡፡ ከዚህ ሥርዓትም በዓላት በአከባር የተለያዩ መኾቸውንና ልዩ የበዓል ቀኖችም እንዳሉ እንረዳለን፡፡ በመጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ ምዕራፍ ፴፥፳፮ ላይ ‹‹በኢየሩሳሌም ታላቅ ደስታ ኾነ፤ ከእስራኤል ንጉሥ ከዳዊት ልጅ ከሰሎሞን ዘመን ጀምሮ እንደዚህ ያለ በዓል በኢየሩሳሌም አልተደረገም ነበር፤›› ተብሎ የተጻፈው ኃይለ ቃል ለዚህ ማረጋገጫችን ነው፡፡
በዓላትን አለማክበር ምንን ያመጣል?
፩. ረድኤተ እግዚአብሔርን ያርቃል
በሰቆቃወ ኤርምያስ ምዕራፍ ፩፥፬ ላይ ‹‹ዳሌጥ፣ ወደ ዓመት በዓልም የሚመጣ የለምና የጽዮን መንገዶች አለቀሱ፡፡ በሮችዋ ዅሉ ፈርሰዋል፡፡ ካህናቶችዋም እየጮኹ ያለቅሳሉ፤ ደናግሎችዋም ተጨነቁ፡፡ እርስዋም በምሬት አለች፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ በዓላትን በማክበራችን ከእግዚአብሔር በረከትን እንደምንቀበል ዅሉ ባለማክበራችን ደግሞ ረድኤተ እግዚአብሔር ከእኛ ይርቃል፡፡
፪. ቅጣትን ያስከትላል
በመጽሐፈ ሳሙኤል ካልዕ እንደ ተገለጸው የእግዚአብሔር ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ በገባ ጊዜ ነቢዩ ዳዊት በደስታ ምስጋና ያቀርብ ነበር፡፡ ሚስቱ ሜልኮል ግን ሲዘምር ባየችው ጊዜ ንጉሥ ኾኖ ሳለ ራሱን አዋረደ በሚል ሐሳብ ባለቤቷ ንጉሥ ዳዊትን ናቀችው፡፡ ዳዊትም ሜልኮልን ‹‹በእግዚአብሔር ፊት ዘፍኛለሁ፤ በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ አለቃ እኾን ዘንድ ከአባትሽ እና ከቤቱ ዅሉ ይልቅ የመረጠኝ እግዚአብሔር የተባረከ ይኹን፡፡ ስለዚህም በእግዚአብሔር ፊት እዘምራለሁ፤›› በማለት ለእግዚአብሔር ምስጋና ማቅረብ እንደሚያስከብርና ከፍ ከፍ እንደሚደርግ ተናግሯል፡፡ እግዚአብሔርም ለአምላኩ የዘመረውን ዳዊትን በመናቋ ልጅ እንዳትወልድ የሜልኮልን ማኅፀን ዘግቶታል /፪ኛ ሳሙ. ፮፥፲፮-፳፫/፡፡ ከዚህ ታሪክ በዓሉን ብቻ ሳይኾን በዓሉን የሚያከብሩ ሰዎችንም ማክበር እንደሚገባን እንማራለን፡፡ ‹‹ዕልልታን የሚያውቅ ሕዝብ ምስጉን ነው፤›› እንዳለ ቅዱስ ዳዊት /መዝ.፹፱፥፲፭/፡፡
በክብረ በዓላት ምን ዓይነት ልብስ መልበስ አለብን?
ሰው ወደ ሰርግ ሲጠራ ከቤቱ ያለውን፣ የተሻለውን ልብስ መርጦ እንዲለብስ መንፈሳውያን በዓላት የቤተ ክርስቲያን የክብሯ መግለጫ ቀናት እንደ መኾናቸው መጠን እኛ ክርስቲያኖችም በእነዚህ ቀናት የምንለብሰው ልብስ የተለየ መኾን ይገባዋል፡፡ የሌሊት ልብስ ለብሶ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሔድ እንደማይገባ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ተደንግጓል፡፡ በገዳማውያን አባቶች ዘንድ ለቅዱስ ቍርባን መቀበያ የሚኾን ልብስ ከሌሎች አልባሳት ተለይቶ ውኀ፣ ጭስ፣ አቧራ ከማይደርስበት ቦታ ይቀመጣል፡፡ አባቶች ይህንን ልብስ የሚለብሱት ለቅዱስ ቍርባን ብቻ ነው፡፡ በገጠሩ የአገራችን ክፍልም ልጆች ልብስ የሚገዛላቸው በአብዛኛው በጥምቀት ወቅት ነው፡፡ ይህም ለበዓሉ የሚሰጠውን ልዩ ክብር ያስረዳናል፡፡ እናቶቻችንም ‹‹ለጥምቀት ያልኾነ ቀሚስ ይበጣጠስ›› እያሉ በበዓለ ጥምቀት ያላቸውን አዲስ ቀሚስ አውጥተው ይለብሳሉ፡፡
በዓመት በዓል ቀን እንስሳት የሚታረዱት ለምንድን ነው?
በዓል ሲደርስ ገበያው ይደምቃል፤ ቤታችን ያምርበታል፡፡ እንበላቸው ዘንድ የተፈቀዱ እንስሳት ይታረዳሉ፡፡ በተለይም በገጠሩ የሀገራችን ክፍል ለፋሲካ፣ ለልደት እየተባለ በግ ተቀጥቅጦ  ይቀመጥና ጊዜው ሲደርስ ይታረዳል፡፡ በበዓላት ቀን የከብት፣ የበግ፣ የፍየል መሥዋዕት ይቀርብ እንደ ነበር መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል፡፡ መጽሐፈ ዕዝራ ፫፥፬ ‹‹እንደ ተጻፈውም የዳስ በዓል አደረጉ፤ እንደ ሥርዓቱም ለዕለቱ የተገባውን የየዕለቱን የሚቃጠል መሥዋዕት በቍጥር አቀረቡ፤›› ይላል፡፡ ዛሬም በበዓላት ቀን በየቤተ ክርስቲያኑ እና በየቤቱ የሚታረደው ይህንኑ አብነት በማድረግ ነው፡፡ (በተጨማሪም ዘሌ.፳፫፥፴፯፤ ሕዝ.፵፮፥፲፩ ይመልከቱ)፡፡
በአጠቃላይ በዓላትን ከሥጋዊ ሥራ ተከልክሎ ማክበር እንደሚገባ ቅዱሳት መጻሕፍት ይናገራሉ፡፡ ‹‹በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይኹንላችሁ፤ የተግባር ሥራ ዅሉ አትሥሩበት፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ /ዘሌ.፳፫፥፯/፡፡ የበዓላት አከባበርም እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ በኾነ ባህል ሳይኾን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን በጠበቀ፤ የበዓሉን መንፈሳዊ ታሪክ በተመረኮዘ መንገድ የተሰጠን ትእዛዝ ነው፡፡ ዮሴፍ ወልደ ኮሪዮን በዜና አይሁድ መጽሐፉ እንደ ጠቀሰው አይሁድ በዕለተ ሰንበት ወደ መጸዳጃ ቤት እንኳን አይሔዱም ነበር፡፡ እኛ ግን እንደ አይሁዳውያን በተጋነነ መንገድ ሳይኾን ሰውነትን ከሚያደክም ሥጋዊ ሥራ ተከልክለን በዓላትን እንድናከብር በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ተደንግጓል፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ አስቀድማ በሕገ ልቦና እግዚአብሔርን ስታመልክ የኖረች በኋላም መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕፀ መስቀሉ የቀደሳት፣ በኪደተ እግሩ የባረካት አገር ናት፡፡ ኢትዮጵያውያን ምእመናን ከጥንት ጊዜ ጀምሮ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርገው መንፈሳውያን በዓላትን በሥርዓት ሲያከብሩ ኖረዋል፡፡ አሁን አሁን ግን በብዙዎቻችን ዘንድ እንደሚስተዋለው የበዓላት አከባበር ሥርዓት እየተጣሰ ይገኛል፡፡ በበዓላት ቀን ሥራ መሥራት እየተለመደ መጥቷል፡፡ ይህ ልማድ ሊስተካከልና ሊቀረፍ ይገባል፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም እንደ በዓለ ጥምቀት ባሉ የዐደባባይ በዓላት ወቅት የሚታየው የሥጋዊ ገበያ ግርግር ክርስቲያናዊ የበዓላት አከባበር ሥርዓትን እንዳያጠፋብን ልንጠነቀቅ ያስፈልጋል፡፡
በአገራችን ብሂል ‹‹በዓል ሽሮ የከበረ፣ ጦም ገድፎ የወፈረ የለም›› እንደሚባለው በዓላትን መሻር ከሚሰጠው ትርፍ ይልቅ የሚያመጣው መቅሠፍት ይብሳልና በዓላትን ለሥጋዊ ጉዳይ መጠቀሚያ ከማድረግ ይልቅ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን መሠረት አድርገን በአግባቡ ማክበር ይገባናል፡፡ አንድ ክርስቲያን መንፈሳውያን በዓላትን በሥርዓት ሲያከብር የሚመለከቱ አካላት ‹‹ሃይማኖቱ እንዴት ደስ ይላል? እኛም እንደ እርሱ በኾንን›› በማለት እርሱንም ሃይማኖቱንም ያደንቃሉ፤ መንፈሳዊ ቅናትንም ይቀናሉ፡፡ ስለዚህም የጥንቱን ሥርዓት ጠንቅቀን፣ መልኩን ሳንለውጥ፣ ሥርዓቱንም ሳናፋልስ በዓላትን ማክበር ይገባናል፡፡ በዓላትን በሥርዓቱ አክብረን በረከትን እናገኝባቸው ዘንድ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

መንፈሳውያን በዓላት እና አሉታዊ አስተሳሰቦች – ክፍል አንድ

ketera1
በዳዊት አብርሃም
የካቲት ፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
በዓል ‹‹አብዐለ-  አከበረ፤ አስከበረ›› ከሚለው ግስ የወጣ ሲኾን ትርጕሙም የደስታ፣ የዕረፍት ቀን፤ ያለፈ ነገር የሚታሰብበት፤ ሕዝብ የበዓሉን ምሥጢር እያሰበ ደስ ብሎት፣ ለብሶ፣ አጊጦ የሚዘምርበት፤ ዕልል የሚልበት ማለት ነው (ኪ.ወ.ክ. ገጽ ፪፸፰-፪፸፱)፡፡ ከዚህ መዝገበ ቃላዊ ፍቺ በርከት ያሉ ጽንሰ ሐሳባዊ ትርጕሞችን የምናገኝ ሲኾን የተወሰነቱን እንደሚከተለው እንመልከት፤
በዓላት የሚከበሩ ናቸው
በዓላት ምእመናን ከዘወትር ሥራዎቻቸው አርፈው በምትኩ መንፈሳዊ ተግባራትን በማከናወን የሚያከብሯቸው ናቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ስለ በዓላት አከባበር በተሠራው ቀኖና በበዓላት ወቅት የማይፈጸም መንፈሳዊ ሥራ ስግደት ነው፡፡ ስግደት ሥጋን የሚያደክም ስለኾነ በበዓላት ወቅት አይሰገድም፡፡ ሌሎች መንፈሳዊ ሥራዎች ግን በበዓላት እንዲፈጸሙ ይፈቀዳል፡፡ ተግባረ ሥጋን በበዓላት መተው አስፈላጊ የሚኾንበት ምክንያት መንፈሳዊ ሥራ ለመሥራት እንዲቻል ነው፡፡
በዓላት የደስታ ዕለታት ናቸው
‹‹በዓል የሚያደርጉ ሰዎች የደስታና የምስጋና ቃል አሰሙ›› (መዝ.፵፩፥፭) እንደ ተባለው፤ በዓል የሚያዝኑበት፣ የሚያለቅሱበት፣ ከምግብ የሚከለከሉበት ወይም የሚጾሙበት ዕለት ሳይኾን ደስ የሚሰኙበት፣ በደስታ ውስጥም ኾነው እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑበት ቀን ነው፡፡ ሐዋርያው ያዕቆብ ‹‹ደስ ያለው ይዘምር›› (ያዕ. ፭፥፲፬) እንዳለው የደስታ ቀን በኾነው በበዓል ስብሐተ እግዚአብሔር በስፋት ይቀርባል፡፡
በዓላት የዕረፍት ቀናት ናቸው
ሌሎች ቀናት የሥራ ቀናት ናቸው፡፡ በዓላት ግን ከእነዚህ ከብዙዎቹ ቀናት ተለይተው ሰው ከሥራው (ከተግባረ ሥጋው) የሚያርፍባቸው ዕለታት ናቸው፡፡ የበዓላት ጥንት የኾነችው ቀዳሚት ሰንበት እግዚአብሔር ሥነ ፍጥረትን ፈጥሮ ያረፈባት በመኾኑ እግዚአብሔር ሰዎች እንዲያርፉባት፤ በዕረፍትም ኾነው እንዲያከብሯት አዝዟል (ዘፍ. ፪፥፩-፫)፡፡ ኾኖም ማረፍ ማለት እጅና እግርን አጣጥፎ መዋል ማለት አይደለም፡፡ በዓላት ከተግባረ ሥጋ የሚታረፍባቸው ዕለታት ቢኾኑም በበዓላት ወቅት መንፈሳዊ ሥራ መሥራት ተገቢና አስፈላጊ መኾኑ ‹‹ክርስቲያኖች እንደ አይሁድ በዕለተ ቀዳሚት ሥራ ፈትተው መዋል አይገባቸውም፡፡ ይልቁንም ለክርስቲያን እንደሚገባ ሥራ ሊሠሩ ይገባቸዋል፤›› ተብሎ በፍትሐ ነገሥት ታዝዟል፡፡
በዓላት የመታሰቢያ ዕለታት ናቸው
እግዚአብሔር አምላክ አስቀድሞ ከሥራው ያረፈባትን የሰንበት ዕለት እንድናስባት አዝዞናል፡፡ ተአምራት ያደረገባቸውን፣ እስራኤል ዘሥጋን በግብጽ ባርነት ነጻ ያወጣበትንና የመሳሰሉትን ዅሉ በበዓላት እንዲታሰቡ አዝዟል (መዝ. ፻፲፥፬)፡፡ በሐዲስ ኪዳንም ‹‹ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት›› በማለት አዝዟል (ሉቃ. ፳፪፥፱)፡፡ የፈጣሪን ሥራም ብቻ ሳይኾን ቅዱሳን ጻድቃንንና ሥራዎቻቸውን መዘከር የበዓላት አንዱ ገጽታ ነው፡፡ ‹‹የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል›› ተብሎ መጻፉም ስለዚህ ነው (መዝ. ፻፲፯፥፳፬)፡፡
የበዓላት አከባበር
በዓላት በልዩ ልዩ መንገዶች ይከበራሉ፡፡ በበዓላት የሚከናወኑ መንፈሳዊና ሕዝባዊ ክንዋኔዎች አሉ፡፡ የተወሰኑ በዓላትን ሕዝብ ወደ ዐደባባይ በመውጣት በጋራ ያከብራቸዋል፡፡ አከባበሩም በዋናነት በጋራ ኾኖ የሚፈጸመውን ሥርዓተ አምልኮና የምስጋና ሥርዓት የሚያመለክት ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን እስራኤል ዘሥጋ በዓላትን ሊያከብሩ ወደ ዐደባባይ ሲወጡ ይዘምሩ ነበር፡፡ ይዘምሩዋቸው ከነበሩ ዝማሬያት መካከልም በመዝሙረ ዳዊት ከመዝሙር ፻፲፱ እስከ ፻፴፫ ያሉት የመዝሙር ክፍሎች ይገኙባዋል (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ገጽ ፴፩)፡፡ ክቡር ዳዊትም በታቦቱ ፊት በቤተ መቅደስ ምስጋና የሚያቀርቡ ካህናትን መድቦ ነበር (፩ኛ ዜ.መ. ፲፮፥፬)፡፡
በአገራችን ኢትዮጵያ በዐደባባይ ከሚከበሩ በዓላት መካከል ቤተ ክርስቲያን የምታውቃቸው ሁለት ዋና ዋና በዓላት የሚገኙ ሲኾን እነዚህም በዓለ መስቀልና በዓለ ጥምቀት ናቸው፡፡ ከዐደባባይ በዓላት መካከል በዓለ መስቀል በዩኔስኮ ከማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶች ተርታ ለመመዝገብ የበቃ ታላቅ በዓል ሲኾን ጥምቀትም በዐደባባይ በዓልነቱ ከአማንያኑ በተጨማሪ የብዙዎችን በተለይም የውጪ ቱሪስቶችን በመሳብ ተወዳዳሪ የሌለው ታላቅ በዓል ነው፡፡ ከወር በፊት በድምቀት ያከበርነው በዓለ ጥምቀት ቤተ ክርስቲያናችን ታቦታትን በማውጣት የምታከብረው ዐቢይ በዓል ነው፡፡ ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው የሦስት ዓመት ከሦስት ወር የማስተማር ሥራውን የጀመረው በጥምቀት ነው፡፡ በየዓመቱ የጥምቀት በዓል የሚከበረውም ይህን ምሥጢር ለመዘከርና ለመመስከር ነው፡፡
ጌታችን ያሳየውን ትሕትና እና ለእኛ አርአያ መኾኑን ለመመስከር፣ ለጥምቀት ኀይልን ለመስጠት እንደዚሁም ውኃን ለመቀደስ ቤተ ክርስቲያን በዓለ ጥምቀቱን በየዓመቱ ታከብራለች፡፡ በየዓመቱ ውኃ ዳር ሔዶ ማክበር በየዓመቱ መጠመቅ ተብሎ እንዳይተረጐምና ሰዎችን እንዳያሳስትም ታስተምራለች፡፡ ይህንኑ ትምህርት ለማስገንዘብም ‹‹የጠበሉን መረጨት አይተው በቀድሞ ዘመን ወደ አገራችን መጥተው የነበሩ ኢየሱሳውያን፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ታጠምቃለች ብለው አጥላልተው ጽፈዋል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ይህን የምትፈጽመው ጌታችን ለኛ ብሎ ያሳየውን ትሕትና ለመመስከር፣ የጌታን በረከተ ጥምቀት ለምእመናን ለማሳተፍ እንጂ የተጠመቁትን ምእመናን እየደመለሰች በየዓመቱ አታጠምቅም፤›› ሲሉ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ጽፈዋል (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ታሪክ ገጽ ፻፳፫)፡፡
የጥምቀት በዓል አከባበር ሥርዓት ከሌሎቹ በዓላት የተለየ ነው፡፡ ታቦታቱ ከመንበረ ክብራቸው ወጥተው በበዓሉ ዋዜማ በሕዝብ ታጅበው ወደ ወንዝ ዳር ይወርዳሉ፡፡ በዚያ ዳስ ተጥሎ፣ ከተራም ተከትሮ ሌሊቱን መዘምራኑ በማኅሌት ካህናቱ በሰዓታት እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ያድራሉ፡፡ ይህም ጌታ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ የመሔዱ ምሳሌ ነው፡፡ ሲነጋም ጸሎተ ቅዳሴው ተጠናቅቆ ወደ ወንዙ በመሔድ ጸሎተ አኮቴት ተደርሶ፣ ዐራቱ ወንጌላት ከተነበቡ በኋላ ውኃው ተባርኮ ለተሰበሰበው ሕዝብ ይረጫል፣ ወንዝም ሲሆን ሰዎች እየገቡ ሊጠመቁ ይችላሉ፡፡ በግብጽ ቤተ ክርስቲያንም፣ ከ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት ዓባይ ወንዝ ወርደው በድምቀት ያከብሩት ነበር፡፡ ከዐረቦች መግባት በኋላ ግን ከሊፋዎቹ (ሡልጣኖቹ) ስለከለከሏቸው በቤተ ክርስቲያን ብቻ ለማክበር ተገድደዋል (The Coptic encyclopedia P.1103)፡፡
ከበዓለ መስቀል እና በዓለ ጥምቀት በተጨማሪ ‹‹አሸንዳ›› (‹‹አሸንድዬ››) በመባል የሚታወቀውና በሰሜን ኢትዮጵያ የሚከበረው የዐደባባይ በዓልም ሙሉ በሙሉ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የሚከናወን በዓል ባይኾንም ሕዝቡ በአለባበሱ፣ በአዘማመሩና በሚያደርጋቸው ሌሎች ክዋኔዎች በዓሉ እንደ ሌሎች ሕዝባዊ ባህሎች አረማዊ ወግን ያልተከተለ መኾኑን የሚያመለክቱ ናቸው፡፡
የበዓላት ፋይዳ
በዓላት በቀዳሚነት የሚከበሩት መንፈሳዊ ዓላማ ይዘው ነው፡፡ ኾኖም በዓላት በሕዝብ የሚከበሩ እንደ መኾናቸው ሌሎች ጥቅሞችም አሏቸው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ሰው መሥራት ብቻ ሳይኾን ማረፍም አለበትና በዓላት ለማረፍና ለመዝናናት ጠቀሜታ አላቸው፡፡ በዅሉም ሀገራት ያሉ ሃይማኖታዊ በዓላት ግብይትን በማሳለጥና የገንዘብ ዝውውርን በማፋጠን ለአገር ኢኮኖሚ ማደግ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የመስኩ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ ሌላው የበዓላት ጥቅም ደግሞ ማኅበራዊ ግንኙነትን ማዳበር ነው፡፡ በበዓላት ሰዎች ይገናኛሉ፤ ስጦታዎችን ይለዋወጣሉ፤ ይገባበዛሉ፡፡ በዚህም ማኅበራዊ ግንኙነታቸውን ያዳብራሉ፡፡ በበዓላት ወቅት ችግረኞች ርዳታ ያገኛሉ፡፡
ከዚህም በላይ በዓላት ለባህል ግንባታ ለመልካም ዕሴት መፈጠር ምክንያት ኾነው ሊያገለግሉ ይችላሉ፡፡ በዓላት የቱሪስት መስሕቦችም ናቸው፡፡ እንደ በዓለ መስቀል በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያገኙ፣ እንደ ጥምቀት ብዙ ሕዝብን የሚያሳትፉ በዓላት የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ከመፍጠራቸውም ባሻገር የውጪ አገር ሰዎች ብዙ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው መጥተው እንዲጐበኙ ዕድል ይፈጥራሉ፡፡ በዚህም አገር የውጪ ምንዛሪ ታገኛለች፡፡ ከዅሉም በላይ በዓላት የአገርን ገጽታ ይገነባሉ፡፡ በተለይ ኢትዮጵያን በመሰለች ስሟ በድርቅና በረኀብ ለምትነሣ አገር በዓላት መጥፎ ገጽታንና ክፉ ስምን የሚቀይሩ ፍቱን መድኀኒቶች ናቸው፡፡
ስለ በዓላት አሉታዊ አስተሳሰቦች
የቤተ ክርስቲያን በዓላት የተጠቀሱትና ሌሎች ያልተጠቀሱ በርካታ ጥቅሞች እንዳሏቸው የታወቀ ቢኾንም አንዳንድ ወገኖች ግን በማወቅም ይኹን ባለማወቅ በዓላትን የሚዘልፉና የሚያንቋሽሹ ወይም የበዓላቱን ዓላማ የሚቃረኑ ሐሳቦችን ያዛምታሉ፡፡ በዚህ ጽሑፍ ከእነዚህ የተቃርኖ ሐሳቦች መካከል ጥቂቶቹን በመጥቀስና የሐሳቦቹን ድክመት በማሳየት ምላሽ እንሰጥባቸዋለን፤
ይቆየን

መንፈሳውያን በዓላት እና አሉታዊ አስተሳሰቦች – ካለፈው የቀጠለ

ketera1በዳዊት አብርሃም
የካቲት ቀን ፳፻፱ .
ስለ በዓላት አሉታዊ አስተሳሰቦች
፩. በዓላት ድህነትን ያስፋፋሉ
በዓላት ድህነትን ያስፋፋሉ የሚሉ ወገኖች እንደ ምክንያት የሚያነሡት በበዓላት ሰዎች ከተግባረ ሥጋ ታቅበው ረፍት ስለሚያደርጉ የሥራ ሰዓት ይባክናል የሚል ነው፡፡ በተጨማሪም ለበዓላት የሚወጡ ወጪዎች ቍጠባ እንዳይኖር ያደርጋሉ በሚል መነሻ በዓላት ድህነትን ያባብሳሉ ብለው ይደመድማሉ፡፡ አስቀድመን እንደ ተመለከትነው በበዓላት ተግባረ ሥጋ ቢከለከልም መንፈሳዊ ሥራና በጎ አድራጎት አልተከለከለም፡፡ ተግባረ ሥጋም ቢኾን በዅሉም በዓላት በእኩል ደረጃ የተከለከለ አይደለም፡፡ መከልከሉም ደግሞ የሰው ልጅ ዕረፍት ስለሚያስፈልገው ነው፡፡ የሰው ልጅ ክቡር ፍጡር እንደ መኾኑ ዅልጊዜ እንደማሽን ሊሠራ ይገባዋል ማለት ሰብአዊ ክብርን የሚያንኳስስ አቋም ነው፡፡
ሠራተኛ ዕረፍት ማድረጉ ለበለጠ ሥራ ያነሳሣዋል እንጂ አያሰንፈውም፡፡ ዕረፍት ካደረጉ በኋላ የሠሩት ሥራ ደግሞ የበለጠ ጥራት ይኖረዋል፡፡ ሰው ዅልጊዜ ያለ ዕረፍት ሊሠራ ይገባዋል የሚሉ ወገኖች ሰዎችን እንደ ሰው ከመቍጠርና ከማክበር ይልቅ እንደ ቍስ የሚቈጥሩና ርኅራኄ የሌላቸው ናቸው፡፡ ሥራዎች የሚሠሩት በሰዎች ብቻ ሳይኾን ለሰዎችም ተብለው መኾኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ከባሪያ ፍንገላ ዘመን ጀምሮ በዘመናችን እስከሚገኘው ጭፍን የሀብት ማጋበስ ዘመን ድረስ ሰው ለጥቂት ባለ ሀብቶች የማይጠግብ ምኞት ቁቍስ አምራችና ገንዘብ ፈጣሪ እንዲኾን የሚያስገድደው ዓለማዊው ሥርዓት የሰውን ክብር የሚያሳውቀውን የክርስትና እምነት መቃወሙ አይገርምም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሰው መሥራት እንዳለበት ታስተምራለች፤ በዚያውም መጠን ዕረፍት እንደሚያስፈልገው ታምናለች፡፡
፪. መንፈሳውያን በዓላት ‹‹ካርኒቫል›› ናቸው
መንፈሳውያን በዓላት የሥጋዊ ደስታ መፍጠሪያ መንገዶች እንዲኾኑና ዓለማዊነት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲገባ የሚፈልጉ ወገኖች እንደ ጥምቀት ያሉ ክርስቲያንናዊ በዓላት በምዕራቡ ዓለም እንደሚታዩት ዓይነት በአብዛኛው ከባዕድ አምልኮ ጋር የተያያዘ የጀርባ ታሪክ እንዳላቸው በዓላት በስካርና ቅጥ ባጣ ፈንጠዝያ እንዲከበሩ ይፈልጋሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የበዓላቱን መንፈሳዊነት አጥፍተው በዓላቱን ፍጹም ዓለማዊ በማድረግ በዓሉ ከሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንጻር ብቻ ሲመለከቱት ልብ ያላሉት ሌላ ነገር በዚህ መልኩ በዓላት መከበራቸው ሥርዓት አልባነትን እንደሚያነግሡና የሥነ ምግባር ውድቀት እንደሚፈጥሩ ነው፡፡ በዚህ መልክ የሚከበሩ በዓላት በምዕራቡ ዓለም ማኅበራዊ ቀውስን ሲፈጥሩ ይታያል፡፡ ከዅሉም በላይ ደግሞ በዓላቱ እውነተኛ ማንነታቸውን ካጡ የቱሪስት መስሕብ መኾናቸውም እንደሚቀር መታሰብ አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ጥንታውያን በዓላት ‹‹ካርኒቫል›› ከኾኑማ አንድ ቱሪስት በዚያው በገዛ አገሩ እያለለት ለምን እኛ ዘንድ ይመጣል? ብሎ መጠየቅ ጉዳዩን በጥሞና ለማየት ይጠቅማል፡፡ (‹‹ካርኒቫል›› በዘፈን፣ በጭፈራ፣ ወዘተ በመሳሰሉ ዓለማዊ ባህሎች የሚከበር የአረማውያን በዓል ነው፡፡)
፫. በዓላት ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘታቸው መንፈሳዊነታቸውን ይቀንሰዋል
ዛሬ ላይ ያለችው ዘመናዊቷ ዓለም በምዕራባውያን ተጽዕኖ ሥር ያለች በመኾኗ ሳቢያ ምዕራባውያኑ የጐሰቈለ የሥነ ምግባር አቋማቸውን በዓለም አቀፍ ተቋማት በኩል እንዲሠራጭ ያደርጋሉ የሚል ስጋት ያላቸው ወገኖች ልክ የመስቀል በዓል እንደ ኾነው ዅሉ በዓላቱ ዩኔስኮን በመሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ዕውቅና ማግኘታቸውን በበጎ አያዩትም፡፡ የእኛም ቤተ ክርስቲያን እንደ ሌሎች ቤተ እምነቶች ወደ ዓለማዊነት ትንሸራተታለች ብለው ይፈራሉ፡፡ በእርግጥ ለቤተ ክርስቲያን ማሰብና ዓለማዊ ዝንባሌዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዳይገቡ መጠንቀቅ ተገቢና አስፈላጊ ነገር ነው፡፡
ኾኖም ጠቃሚ ነገሮችን በይኾናል ስጋት ተሸብረን እንዳናስቀራቸው መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ ዓለም አቀፍ ተቋማት ኢ ክርስቲያናዊ ሐሳቦችን መያዛቸው፣ እነዚህን ሐሳቦች እንደ ሕግ መቀበላቸውና ሀገራት እነዚህን እኩይ ሐሳቦቻቸውን ተቀብለው እንዲሠሩባቸው ጫና መፍጠራቸው ቤተ ክርስቲያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለ መንቀሳቀሷ የተፈጠረ ክፍተት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖዋን ለማሳረፍ ብትሠራ ዓለም እንደማያሸንፋት ጌታችን ቃል ገብቶላታል፡፡ ስለዚህ መንፈሳዊ በዓሎቻችን በዓለም አቀፍ ተቋማት ዕውቅና ማግኘታቸው በጎ እንጂ ክፉ አይደለም፡፡ ሥጋቶችን ወደ በጎ ዕድሎች የመቀየር አንዱ ዘዴ በመኾኑ ይህ ጥረት በሌሎች ዘርፎችም ሊቀጥል ይገባል፡፡
፬. በበዓላት የምእመናንን ሱታፌ የሚገድቡ አመለካከቶች
በቤተ ክርስቲያን ዅሉም አካላት ልዩ ልዩ ድርሻ አላቸው፡፡ ካህናቱና ሊቃውንቱ ብቻ አገልግለው ሌላው ምእመን ተመልካች አይኾንም፡፡ በበዓላትም ምእመናን በልዩ ልዩ መንገድ ያገለግላሉ፤ በዓሉን ያደምቃል፡፡ ለምሳሌ በበዓለ ጥምቀት ምእመናን ለየት ባሉ ግጥሞችና ዜማዎች እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ እንሰማለን፡፡ አንዳንድ ዘመን አመጣሽና ጥሩ ያልኾኑ ነገሮች በመጠኑ ቢታዩም በአብዛኛው የሕዝቡ ባህል ክርስቲያናዊ ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ ታዳጊ ወንዶችና ልጃገረዶች በቡሄና ዘመን መለወጫ በዓላት የሚያዜሙት ዜማ ጠፍቶባቸው፣ ግራ ተጋብተው የምናየው ባህሉ በወጉ ለትውልድ መተላለፍ ባለመቻሉ ነው፡፡ ቀስ በቀስም ‹‹ነይ ነይ እምዬ ማርያም›› የሚለው የእናቶች ዜማ እየተዘነጋ እንዳይመጣ ያሰጋል፡፡ ስለኾነም ከዓለማዊ ዘፈን እና ከባዕድ ባህል ነጻ የኾኑ የሕዝብ የምስጋና ወይም የአገልግሎት ተሳትፎዎች ሊበረታቱ እንጂ ሊነቀፉ አይገባም፡፡
፭. በዓላትን በዓለማዊነት ፈለግ የማክበር ዝንባሌ
መንፈሳውያን በዓላት ከቤተ ክርስቲያን ያገኘናቸው፣ ታላላቅ መንፈሳዊ ትርጕሞችን ያዘሉ፣ ሰማያዊ ምሥጢራትን የያዙ፣ እኛን ከመለኮታዊ መገለጥ ጋር ድልድልይ ኾነው የሚያገናኙን ዕለታት ናቸው፡፡ እነዚህን በዓላት ከዓለም እንደ ተገኙ ዅሉ በዓለማዊ መርሐ ግብሮች ማክበር ከክርስቲያኖች አይጠበቅም፡፡ ከዚያም አልፎ አብዝቶ በመብላትና በመጠጣት፣ በመስከር ቅጥ ባጣ ፈንጠዝያ ማሳለፍ የበዓሉን ትርጕም ማዛባት ነው፡፡ በዓላት በሥርዓተ አምልኮ፣ በማኅሌት በቅዳሴ፣ በዝማሬ፣ በቃለ እግዚአብሔር፣ በክርስቲያናዊ ፍቅርና አንድነት፣ አብሮ በመብላት፣ ችግረኞችን በማስታወስ ሊከበሩ እንደሚገባው የቤተ ክርስቲያን የዘወትር ትምህርቷና ትእዛዟ ነው፡፡
፮. ክርስቲያናዊ በዓላትን ከባዕድ አምልኮ ጋር ማሻረክ
ክርስትና ጣዖትን ያጠፋ ሃይማኖት ነው፡፡ በጥንት ጊዜ በምዕራቡ ዓለም የጌታ ልደት በሚከበርበት ሰሞን ‹‹የፀሐይ ልደት›› እየተባለ የሚታሰብ የጦኦት አምልኮ ነበር፡፡ ሊቃውንቱ አማናዊው ፀሐይ ክርስቶስ ነውና በዚህ ዕለት የጌታችን ልደት እንዲከበር በማድረግ የሕዝቡን ልብ ከአምልኮ ጣዖት ወደ አምልኮ እግዚአብሔር መልሰውታል፡፡ በአገራችንም የመስቀል በዓል በሚከበርበት ሰሞን በደቡብ አካባቢ ይታሰብ የነበረውን ጣዖት አምልኮ ጻድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ ካስወገዱ በኋላ በምትኩ የጌታችን መስቀል መገኘት መከበር መጀመሩ የሕዝቡን ልብ ከጣዖት አምልኮ እንዲርቅ አድርጎታል፡፡ የሰው መንፈስ ሲዝል ግን የጠፋው ባዕድ አምልኮ ያንሰራራል፡፡ ሰይጣንም ይህን ለማድረግ አይተኛም፡፡ የተሻሩ ጣዖታት አንዳንድ ጊዜ መንፈሳዊ በዓላት ላይ ጥላቸውን ያጠላሉ፡፡ በእመቤታችን ልደት ባዕድ አምልኮን የሚደብሉ፣ በሊቃነ መላእክት በዓላት ላይ በጠንቋይ ታዘው ዝክር የሚዘክሩ ሰዎች አሉ፡፡ እንደዚሁም በመስቀልና በጥምቀት በዓላት ላይ ለሰይጣን የሚሰዉ ዅሉ ቤተ ክርስቲያን የሰጠቻቸውን ክርስቲያናዊ በዓላት አርክሰዋልና በንስሐ ሊመለሱ፤ ለወደፊቱም ሊጠበቁ ይገባል፡፡
፯. የባዕድ በዓላትን ሳይመረምሩ መቀበል
በየጊዜው ከውጪ ሀገራት በተለይም ከምዕራባዊው ዓለም የሚገቡ በዓላት በዘመናችን ቍጥራቸው እየበዛ ነው፡፡ የእነዚህ ምዕራባዊ ባህሎች ተጽዕኖ ወደ ኢትዮጵያም በመዝለቅ ላይ ነው፡፡ ለአብነትም ‹‹ሀሎዊን›› በመባል የሚያታወቅ ከባዕድ አምልኮ ጋር የተቆራኘ፣ ክርስቲያኖች ሊያከብሩት የማይገባ የአሕዛብ በዓል በውጪ አገር በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ከመከበር አልፎ በአገራችንም በአንዳንድ ቦታዎች መከበር መጀመሩ አሳሳቢ ነው፡፡ እንደዚሁም የጌታችንን ልደት በአገራችን የቀን አቈጣጠር ማክበር በቂ ኾኖ ሳለ ‹‹የፈረንጆች ገና›› እያሉ ማክበር ትክክል አይደለም፡፡
፰. የበዓል አከባበርን በባዕዳን ተጽዕኖ መቀየጥ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በዓላት በዋዜማ ይጀምራሉ፡፡ ማኅሌት ተቁሞ ስብሐተ እግዚአብሔር ይደርሳል፡፡ ካህናትና ምእመናን በሥርዓት ለብሰው በቤተ መቅደሱ በመገኘት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ያድራሉ፡፡ በበዓሉ ቀንም በየቤታቸው እየተገባበዙ ደስ ብሏቸው ይውላሉ፡፡ አሁን አሁን ግን የበዓሉን ዋዜማ በመሸታ ቤት፣ በዳንኪራና በስካር ማክበር እየተለመደ ስለመጣ ዋዜማን እኛጋ አክብሩ የሚሉ ጥሪዎች ከተለያዩ መዝናኛ ቦታዎች ይጎርፋሉ፡፡ ከዚህም ውጪ ‹‹የገና ዛፍ›› እንደሚባለው ያለ በእኛ ባህል ትርጕምም፣ ጥቅምም የሌለው እንዲያውም ባዕድ ከመኾኑም በላይ የተፈጥሮ ሀብትን የሚያወድምና አካባቢን የሚያራቁት ተግባር በመፈጸም ፈርጀ ብዙ ቀውስ ማድረሳችንን ማቆም አልቻልንም፡፡
፱. በዓላትን የሚያጥላሉ የመናፍቃን አስተሳሰቦች
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እምነት፣ ሥርዓትና ትውፊት ማጥላላትና ማጠልሸት እንደ ዋና ሥራና ግብ አድርገው የሚሠሩ መናፍቃን በቤተ ክርስቲያን አጽዋማት ላይ ተቃውሞ እንደሚያነሡት ዅሉ በበዓላቶቿም ላይ የመረረ ተቃውሞን ይሰነዝራሉ፡፡ የመናፍቃኑ ተቃውሞ መጽሐፍ ቅዱስን በጭንብልነት የተጠቀመ ቢመስልም ምንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃና መነሻ የሌለው ከመኾኑም በላይ እንዲያውም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጣረስና በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የምናውቀውን የቤተ ክርስቲያንን ትውፊት ያፋለሰ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በመናፍቃኑ ሐሳብ እንዳይወሰዱ ወደ ቤተክርስቲያን ቀርበው ሊማሩ፤ ጥያቄዎችን ለመምህራን አቅርበው መልስ ሊያገኙ፤ ስለ በዓላት የተጻፉ መጻሕፍትንም ሊያነቡ ይገባል፡፡ ያ ካልኾነ ግን በዕውቀት ማጣት ምክንያት በመናፍቃን ወጥመድ መያዝና መሳት ይመጣል፡፡
፲. በዓላትን ለወቅታዊ ኹኔታዎች ማስገዛት
አንዳንድ ጊዜ በዓላት በሌሎች ውጫዊ አጀንዳዎች ሲጠመዱ ይታያል፡፡ ለወቅታዊ የአረማውያን ጥቃት ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ጽሑፎች የለጠፉ ልብሶችን (ቲ ሸርቶችን) በመልበስ፣ የዛቻና የማስፈራሪያ ይዘት ያላቸው ‹‹የካሴት›› መዝሙሮችን በማሰማት በዓላትን ማክበር አንዱ ችግር ነው፡፡ ሌላው ችግር መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት፣ የፖለቲካ ቡድኖች፣ ወዘተ. የሚፈጥሩትን አጀንዳ ተሸክሞ በማሰብም ይኹን ባለማሰብ በመንፈሳዊ በዓላት ላይ ማቀንቀን፣ ‹‹ለመቻቻል›› እየተባለ ክርስቲያናዊ ያልኾኑ በዓላትን ማክበር ብዙ ጠንቅ አለው፡፡ ከኹሉም በላይ ደግሞ ሸቀጣቸው እንዲነሣላቸው የሚፈልጉ ነጋዴዎች የሚፈጥሯቸው በዓላትና የበዓላት አከባበሮች ክርስቲያኖችን የሸቀጥ ሰለባ እንዳያደርገን መጠንቀቅ አለብን፡፡ በአጠቃላይ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በዓላትን ስታከብር ሕግን ጠብቃና ሥርዓትን ሠርታ ስለኾነ ምእመናን በዓላትን በምናከብርበት ጊዜ ከኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ እንዳንወጣና ሥርዓቱንም እንዳናፋልስ መጠንቀቅ ይገባናል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች!
ይህ ጽሑፍ በጥር ወር ፳፻፱ ዓ.ም በወጣው ፳፬ኛ ዓመት ቍጥር ፱ የሐመር መጽሔት ዕትም፣ ገጽ ፲፬ – ፲፯፤ ‹‹ቤተ ክርስቲያን የሰጠችንን በዓላት እንዴት እናክብራቸው?›› በሚል ርእስ ለንባብ መብቃቱን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡ 

ሱባዔና ሥርዓቱ / መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ


ያለንበት ወቅት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ጾመ ፍልሰታን የሚጾሙበት ሱባዔ የሚገቡበት ወቅት ነው፡፡ ለዚህ ወቅት ምእመናን ዝግጅት እያደረጉ ነው፡፡መልካም የሱባዔ ጊዜ ይሁንልን፡፡
ሱባዔ ምንድን ነው?
ሱባዔ በሰዋስው ትርጉሙ ሰባት ማለት ነው፡፡ ሱባዔ በመንፈሳዊ አተረጓጎም አንድ ሰው ከዚህ ቀን እስከዚህ ቀን በጸሎት ከፈጣሪዬ እገናኛለሁ ብሎ የሚያቅደው መንፈሳዊ ዕቅድ ነው፡፡ ሰባት ቁጥር በእስራኤላውያን ዘንድ በሥራም በቃልም የሚገለጥ ፍጹም ቁጥር ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔር በሰባተኛው ቀን ሥነ ፍጥረትን ከመፍጠር ማረፉ፣ ለጸሎት የሚተጉ ምእመናን በቀን ለሰባት ጊዜ ማመስገናቸው የሰባት ቁጥርን ፍጹምነት ያመለክታል፡፡ ዘፍ.2፥2፤ መዝ.118፥64፡፡ ከዚህ አንጻር አንድ ሰው ለሰባት ቀናት ቢጾም አንድ ሱባዔ ጾመ ይባላል፡፡ ለዐሥራ አራት ቀን ቢጾም ሁለት ሱባዔ ጾመ እያለ እየጨመረ ይሄዳል፡፡
መቼ ተጀመረ?
ሱባዔ የተጀመረው ከውድቀት በኋላ በመጀመሪያው ሰው በአዳም ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት አዳምን ጸሎት መጸለይን እንዳስተማሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡መላእክት ለአዳም ጊዜያትን አስተምረውት ነበር፡፡ ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ፡፡ አዳም ጥፋቱን አምኖ ከባሕር ውስጥ ሱባዔ በመግባቱና በመጸለዩ እግዚአብሔር በማይታበል ቃሉ ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንኀለሁ ሲል ቃል ኪዳን ገብቶለታል /መጽሐፈ ቀሌምጦስ አንቀጽ አራት/፡፡
ሱባዔ ለምን?
የሰው ልጅ ኃጢአት በሚስማማው የሥጋ ሰውነቱ ዘወትር ፈጣሪውን ይበድላል፡፡ በፈጸመው በደል ኅሊናው ይወቅሰዋል፡፡ ይጸጸታል፡፡ በመጀመሪያ ደፍሮ በሠራው ኃጢአት በኋላ ይደነግጣል፡፡ ይህ በማንኛውም ሰብአዊ ፍጥረት ኅሊና ውስጥ የሚፈራረቅ ክስተት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ የፈጣሪውን ይቅርታ ለማግኘት ያስባል፤ ይተክዛል፡፡በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛል. ነገር ግን በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝ ሌላ ሕግ አያለሁ፡፡ እኔ ምንኛ ጐስቋላ ሰው ነኝ ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል? እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ ሮሜ.7.22-25፡፡
ሰው በደፋርነቱ የኃያሉን አምላክ ትእዛዝ ተላልፎ ትካዜ ሽክም ሲያስጨንቀው ሸክሙን የሚያቃልልበትና የሚያስወግድበት መንፈሳዊ ጥበብ ከቸሩ ፈጣሪ ተሰጥቶታል፡፡ ይኸውም በጥቂት ድካመ ሥጋ ጸጋ እግዚአብሔር የሚያገኝበት ሥርዓት ሱባዔ ነው፡፡ ከጥንት እስከ ዛሬ አንድ ሰው በትካዜ ሽክም መንፈሱ ሲታወክ የነፍስና የሥጋ ጸጥታውን ለመመለስና ለማስከበር መጾምና መጸለይ ግድ ይሆንበታል፡፡ በዚህ ጊዜ አመክሮ /ሱባዔ/ ይገባል፡፡
እግዚአብሔርን ለመማፀን
ሰው ሱባዔ ከሚገባባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱ እግዚአብሔርን ለመማፀን ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ሱባዔ ሲገባ በቁርጥ ወደ ፈጣሪው የሚያቀርበው ተማኅፅኖ ሊኖረው ይገባል፡፡ ምንም የምንጠይቀው /የምንማፀነው/ ነገር ሳይኖር ሱባዔ ብንገባ የምናገኘው መልስ አይኖርም፡፡ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታና ዝግጅት ሱባዔ የሚገቡ ሰዎች ከሱባዔ በኋላ ምን እንደ ተመለሰላቸው የሚያውቁት ነገር ስለማይኖር ሱባዔ በመግባታቸው የሚያገኙት ነገር የለም፡፡
ስለዚህ ሱባዔ ከመግባታችን በፊት፡- ሱባዔ የምገባው ለምንድን ነው? በማለት ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ክርስቲያን በግል ሕይወቱ ዙሪያ ስለ ሀገር ሰላም፣ ስለ ጓደኛው ጤና ወዘተ ጉዳዮች ላይ ፈጣሪውን ይማፀናል፡፡ በዚህ ጊዜ በግል ሕይወቱም ሆነ በሀገር ጉዳይ ለገባው ሱባዔ ወዲያውኑ መልስ ሊያገኝ ይችላል፤ እንዲሁም መልሱ ሊዘገይ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ከተሐራሚው ትዕግሥት /መታገሥ/ ይጠበቅበታል፤ «ለምን ላቀረብኩት ጥያቄ ቶሎ መልስ አልተሰጠኝ?» በማለት ማማረርና እግዚአብሔርን መፈታተን ተገቢ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ሥራውን የሚሠራበትና ለሚማፀነውም መልስ የሚሰጥበት የራሱ ጊዜ አለው፡፡ ለምሳሌ በጓደኛው ውድቀት ምክንያት ሱባዔ ገብቶ በአንድ ሳምንት ውስጥ መልስ ያገኘ የአንድ ገዳም አገልጋይ ታሪክ መመልከት ተገቢ ነው፡፡
አኃው ለተልእኮ በወጡበት አንዱን ድቀት አግኝቶት አድሯል፡፡ በነጋው ወንድሜ እኔ ድቀት አግኝቶኛልና እንግዲህ ወዲህ ተመልሼ ከዚያ ገዳም አልሔድም፤ ሽለሙን መስዬ እኖራለሁ አለው፡፡እኔም እንጂ አግኝቶኛል፤ ይልቁንስ ሔደን ኃጢአታችንን ለመምህረ ንስሐችን ነግረን፤ ቀኖናችንን ተቀብለን እንደ ቀደመው ኾነን እንኖራለን ብሎ አጽናንቶ ይዞት ሔደ፡፡ ሔደው ለመምህረ ንስሐቸው ነግረው ቀኖናቸውን ተቀብለው 1 /አንድ/ ሱባዔ፣ ቀኖና እንዳደረሱ ሰረይኩ ለከ በእንተ ዘኢገብረ እኁከል፤ ኃጢአት ስላላደረገው ወንድምህ ይቅር ብዬሃለሁ የሚል ድምፅ አሰምቶታል፡፡ /ዜና አበው/፡፡
ከላይ ታሪካቸው የሰፈረው የገዳም አገልጋዮች ለአገልግሎት በተላኩበት አገር አንዱ ድቀት አግኝቶት በዝሙት ሲወድቅ ጓደኛው እንደ እርሱ ድቀት እንዳገኘው አድርጐ ጓደኛውን በማጽናናት ወደ ገዳም በመመለስ አንድነት ኾነው ሱባዔ ይገባሉ፡፡ አንድ ሱባዔ /ሰባት ቀን/ እንደ ጨረሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ ኃጢአት ሳይሠራ ለአንተ ብሎ ሱባዔ ስለገባው ወንድምህ ስል ይቅር ብዬሃለሁ የሚል ፈጣን መልስ አግኝቷል፡፡ ስለዚህ ሱባዔ በግል ሕይወትም ሆነ በጓደኛችን ሕይወት ዙሪያ ስንገባ ፈጣን ወይም የዘገየ መልስ ሊሰጠን ስለሚችል በትዕግሥት መጠባበቅ ይኖርብናል፡፡
የቅዱሳንን በረከት ለመሳተፍ
ቅዱሳን አባቶችና ቅዱሳት እናቶች የተጋደሉትን ተጋድሎ በማዘከር ቃል ኪዳን በተሰጣቸው ገዳማትና አድባራት የሚገባ ሱባዔ የቅዱሳኑን በረከት ተካፋይ ያደርጋል፡፡ ቅዱሳን በሚጋደሉበት ቦታ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ ስም እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋ የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ /ኢሳ.56.6/ በማለት እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ስለ ገባላቸው ሱባዔ በመግባት በረከታቸውን መሳተፍ ይቻላል፡፡ በጾመ ነቢያት የነቢያትን በረከት ለመሳተፍ፣ በጾመ ሐዋርያት የሐዋርያትን በረከት ለመሳተፍ፣ በጾመ ፍልሰታ የእመቤታችንን በረከት ለመሳተፍ ሱባዔ መግባት የነበረና ወደ ፊትም የሚኖር የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ነው፡፡ ዛሬ ይህን ሥርዓት በመከተል የተለያዩ ቅዱሳንን በረከት ለመቀበል /ለመሳተፍ/ የቅዱሳን አፅም ካረፈበት ገዳም በጾም፣ በጸሎት፣ በጉልበትም ገዳማትን በማገልገል የቅዱሳንን በረከት ደጅ የሚጠኑ ምእመናንና መናንያን በየገዳማቱ እጅግ በርካታ ናቸው፡፡
ይኸውም በመጽሐፈ ነገሥት ካልዕ በምዕራፍ 2.9 እንደ ተመለከተው ነቢዩ ኤልሳዕ መምህሩን ኤልያስን በማገልገል የኤልያስ በረከት በእጥፉ በኤልሳዕ ላይ አድሮበታል፡፡ ይህን አብነት በማድረግ በየገዳማቱ በትህርምት የሚኖሩ መናንያንን ያገለገሉበትን ገዳም አባት በረከት በእጥፍ እየተቀበሉ ለሌሎችም የሚያቀብሉ አባቶች በየገዳማቱ አሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ሆኖ በስመ ገዳማዊ የምእመናንን ገንዘብ የሚዘርፉና የእውነተኛ መነኮሳትንና መናንያንን የተቀደሰ ሕይወት የሚያጐድፉ መኖራቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
የተሰወረ ምሥጢር እንዲገለጥልን
በዘመነ ብሉይ እግዚአብሔር ለአንዳንድ ነገሥታት ራእይ በማሳየት ምሥጢርን ይሰውርባቸው ነበር፡፡ ለምሳሌ የግብፁን ፈርዖን፣ የባቢሎኑን ናቡከደነፆርንና ብልጣሶርን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ዘፍ.41.14-36፡፡ ዳን.4.9፤ ዳን.5.4፡፡ እነዚህ ነገሥታት በግል ሕይወታቸውም ሆነ በመላው ሽክም ወደ ፊት ሊፈጸም የሚችል ራእይ ቢያዩም ቅሉ ራእዩን በትክክል ተረድተው እንዲህ ይሆናል የማለት ብቃት አልነበራቸውም፡፡ ስለዚህ በዘመናቸው ይኖር የነበሩትን ነቢያት ሱባዔ ገብተው የሕልማቸውን ትርጉም እንዲነግሩአቸው ይማፀኑ ነበር፡፡ ነቢያትም ሱባዔ በመግባት ነገሥታቱ ያዩትን የምሥጢረ ሥጋዌ ነገርና የመንግሥታቸውን አወዳዳቅ ገልጸው ይናገሩ ነበር፡፡ ዳን.5.28፡፡
እንዲሁም ቅዱሳን በየራሳቸው ያዩት ራእይ ምሥጢር ሲከደንባቸው የራእዩ ምሥጢርና ትርጉም እንዲገለጥላቸው ሱባዔ ይገባሉ፡፡ እግዚአብሔርም በንጽሕና ሆነው የገቡትን ሱባዔ ተመልክቶ ምሥጢር ይገልጥላቸዋል፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ዕዝራ የመጻሕፍትን ምሥጢር እንዲገልጥለት ሱባዔ ቢገባ የጠፉትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዳግም መልሶ ለመጻፍ ችሏል፡፡ መዝ.8.1፡፡
ሱባዔ አዳም
አዳም ትንቢት በመናገርና ሱባዔ በመቁጠር የመጀመሪያውን ሥፍራ ይይዛል፡፡ ምክንያቱም በገነት ሰባት ዓመት ከአንድ ወር ከዐሥራ ሰባት ቀን በተድላና በደስታ ከኖረ በኋላ ሕግ በማፍረሱና የፈጣሪውን ቃል በመጣሱ ያለምንም ትካዜና ጉስቁልና ከሚኖርበት ዔደን ገነት ተባርሯል፡፡ ዘፍ.3.24፡፡ እርሱም ፈጣሪው እንዲታረቀው፣ በዐይነ ምሕረት እንዲጐበኘው፣ ቅዝቃዜው ሰውነት ከሚቆራርጥ ባሕር ውስጥ በመቆም ለሠላሳ አምስት ቀን /አምስት ሱባዔ/ ሱባዔ ገብቷል፡፡ በባሕርዩ የሰውን ልጅ እንግልት የማይወድ ቸሩ ፈጣሪ የአዳምን ፈጽሞ መጸጸት ተመልክቶ በሐሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ ወእድኅክ ውስተ መርህብከ ወእትቤዘወከ በመስቀልየ ወበሞትየ በአምስት ቀን ተኩል ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ ብሎ ተስፋውን ሰጠው፡፡ አዳም የተሰጠውን ተስፋ ይዞ በዓለመ ሥጋ ለዘጠኝ መቶ ሠላሳ አመት ከኖረ በኋላ መከራና ችግር ከበዛበት ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡
በወንጀል ተከሶ በወኅኒ የተፈረደበት ሰው ከእስር የሚፈታበትን ዕለት በማውጣት በማውረድ ወራቱንና ዓመታቱን እንደሚቆጥር፣ አዳምም በሞት ቢለይም በሲኦል የነፍስ ቅጣት ካለበት ሥፍራ ይኖር ስለነበር የተሰጠውን ተስፋ በማሰብ ሱባዔውን እየቆጠረ የተናገረውን የማያስቀር የማያደርገውን የማይናገር ጌታየ እነሆ አድንኀለሁ ብሎ የገባልኝ ዘመን ተፈጸመ፤ ሰዓቱ አሁን ነው፤ እያለ ሲያወጣ ሲያወርድ ቸር አምላክ ሰው ኾኖ ሥጋ ለብሶ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ፡-ተንሥኡ ለጸሎት ለጸሎት ተነሡ፤ ሰላም ለኩልክሙ፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን በማለት አዳምን ከነልጅ ልጆቹ ነጻ አውጥቶታል፡፡
ሱባዔ ሔኖክ
ጻድቁ ሔኖክ፣ የያሬድ ልጅ ሲሆን፣ በትውልድ ከአዳም ሰባተኛ ነው፡፡ እርሱም በሕይወቱ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ቤት ንብረቱን በመተው በሱባዔና በትሕርምት እግዚአብሔርን አገልግሏል፡፡ ፍጹም አካሔዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገ ሰው በመሆኑ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን መልካም ግብር ተመስክ ሮለታል፡፡ሔኖክም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ፡፡ ዘፍ.5.22፡፡ ይህም በመሆኑ እግዚአብሔር የሱባዔውን ዋጋ ቅዱስ መንፈሱን በረድኤት ስለ አሳደረበት ትንቢት ተናግሯል፤ ሱባዔ ቆጥሯል፡፡ በሰማይ ተሰውሮ ሳለ ስለ ቅዱሳን መላእክት፣ ስለ መሢሕ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ስለ ፀሐይና ጨረቃ አመላለስ /ዑደት/ የሚተርክ በስሙ የተሰየመውን መጽሐፍ ጽፏል፡፡ ዘፍ.5 21-24፡፡ ይሁዳ ቁ.14፡፡ ሔኖክ 1.9፡፡
ሱባዔ ሔኖክ የሚባለው ነቢዩ ሔኖክ በመስፈርት የቆጠረው ሱባዔ ነው፡፡ መስፈርቱ /ማባዣ ቁጥር/ 35 ሲሆን 35’19 ሲበዛ በውጤቱ 685 ዓመት ይሆናል፡፡ 685’12 ስናባዛው 7980 ይሆናል፡፡ ይኸውም ሐሳብ የሚያስረዳው ስለክርስቶስ ምጽአት ነው፡፡
ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ አሁን የደረስንበት ዘመን 7497 ይሆናል፡፡ ይህን ለማረጋገጥ በ5500 ዓመት ላይ 1997 ዓመትን መደመር ነው፡፡ በዚህን ጊዜ ከላይ ያስቀመጥነውን 7497 ዓመት ይሰጠናል፡፡ በነቢዩ ሔኖክ አቆጣጠር መሠረት ምጽአተ ክርስቶስ በ7980 ይሆናል፡፡ ከላይ ሔኖክ የቀመረውን ቁጥር ይዘን ከ7980 ዓመት ላይ አሁን ያለንበትን ዘመን /1997/ ስንቀንስ 483 ዓመት እናገኛለን፡፡ ስለዚህ በሔኖክ ሱባዔ መሠረት ምጽአተ ክርስቶስ ሊሆን 483 ዓመት ይቀራል፡፡
ሱባዔ ነቢያት
እግዚአብሔር ለአዳም የገባውን ቃል ኪዳን መሠረት በማድረግ ቀደምት ነቢያት በተነሡበት ዘመን ቅደም ተከተል ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆንና ዳግም መምጣት ትንቢት ተናግረዋል፡፡ ሱባዔም ቆጥረዋል፡፡ ኢሳ.7.14፡፡ መዝ.49.3፡፡ ዘካ.13.6፤ ዘካ.14.1፡፡ የአንዱ ነቢይ ትንቢታዊ ንግግርና ሱባኤ በአነጋገርና በአቆጣጠር ከሌላኛው ነቢይ ጋር ይለያያል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ትንቢቱን ሲያናግር ምሳሌውን ሲያስመስል ጐዳናው ለየቅል በመሆኑ ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጐዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ፡፡ እንዲል፡፡ ዕብ.1.1፡፡ የአቆጣጠር ስልታ ቸውና የሱባዔ መንገዳቸው ቢለያይም ዓላማና ግባቸው ግን አንድ ነው፡፡
ሱባዔ ዳንኤል
ነቢዩ ዳንኤል ምድቡ ከዐበይት ነቢያት ነው፡፡ እስራኤል ወደ ባቢሎን ሲማረኩ ተማርኮ ወደ ባቢሎን ወርዷል፡፡ እርሱም ስለ ክርስቶስ መምጣት ትንቢት ተናግሯል፤ ሱባዔም ቆጥሯል፡፡ሰብአ ሰንበታተ አድሞሙ ለሕዝብከ፤ ሰባ ሰንበት ወገኖችህን ቅጠራቸው፡፡ ይኸውም ክርስቶስ ከ490 ዓመት በኋላ ሰው መሆኑን የሚያመለክት ትንቢት ነው፡፡ እንዲሁም እስከ ክርስቶስ ንጉሥ ትትሐነፅ መቅደስ ወእምዝ ትትመዘበር፤ እስከ ንጉሥ ክርስቶስ ድረስ መቅደስ ትታነፃለች በኋላም ትፈርሳለች ሲል ተናግሯል፡፡
የአቆጣጠር ስልቱም በዓመት ሲሆን ይኸውም ሰባቱን ዓመት አንድ እያሉ መቁጠር ነው፡፡ ይኽውም ሱባዔ ሰንበት ይባላል፡፡ ዳንኤል ሱባዔ ከቆጠረበትና ትንቢት ከተናገረበት ጀምሮ ክርስቶስ እስከ ሚወለድ 490 ይሆናል፡፡ መስፈርቱ /ማባዣው/ ሰባት ስለሆነ 7€™70 ስናባዛው 490 እናገኛለን፡፡ ይኸውም ነቢዩ ሱባዔ ከቆጠረና ትንቢት ከተናገረ ከ490 ዓመት በኋላ የክርስቶስን መወለድ ያመለክታል፡፡
በአጠቃላይ ከላይ የተመለከትናቸው ቅዱሳን ነቢያት አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር በማድረግ ሱባዔ ገብተው በትሕርምት በመኖራቸው ድንቅ የሆነውን የክርስቶስን ልደትና ዳግም ምጽአት ለመተንበይ ችለዋል፡፡ ሱባዔ መግባት የራቀን ለማቅረብ የረቀቀን ለማጉላት ብቃትን ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስገኝ መንፈሳዊ ጥበብ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡
ሱባዔ ዳዊት
ነቢዩ ዳዊት ከእስራኤል ነገሥታት ሁሉ ታላቅና ተወዳጅ ንጉሥ ነበር፡፡ ዘመነ መንግሥቱ 1011-971 ከክርስቶስ ልደት በፊት እንደ ነበር ይታመናል፡፡ ነቢዩ ዳዊት ልበ አምላክ እንደ መሆኑ ትንቢት ተናግሯል፡፡ ሱባዔ ቆጥሯል፡፡ ይኽውም ቀመረ ዳዊት በመባል ይታወቃል፡፡እስመ ዐሠርቱ ምእት ዓመት በቅድሜከ፤ ከመ ዕለት እንተ ትማልም ኃለፈት፤ ሺ ዓመት በፊትህ እንዳለፈች እንደ ትላንት ቀን፡፡ /መዝ.89.4/ የሚለውን መምህራን ሲቆጥሩት 1140 ዓመት ይሆናል፡፡ ይኸውም በጌታ ዘንድ 1140 ዓመት እንደ አንድ ቀን እንደሆነ ነቢዩ ዳዊት ተናግሯል፡፡ ይህም ለዳዊት ሱባዔ መቁጠሪያ /መሥፈሪያ/ ሆኖ አገልግሏል፤ 11407= 7980 ዓመት ይሆናል፡፡ ይህም ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በ7980 ዓመት ክርስቶስ ዳግም እንደ ሚመጣ የሚያመለክት ነው፡፡
ሱባዔ በዘመነ ሐዲስ
በዘመነ ሐዲስ በሰፊው የሚወሳው ቅዱሳን ሐዋርያት ከነሐሴ 1-14 የገቡት ሱባዔ ነው፡፡ ይህ ሱባዔ ተሰውሮ የነበረውን የቅድስት ድንግል ማርያምን ትንሣኤ ተረድተው በረከቷን ለመሳተፍ አብቅቷቸዋል፡፡እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሦስት ዓመት በእናት በአባቷ ቤት፣ ዐሥራ ሁለት ዓመት በቤተ መቅደስ ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከጌታችን ጋር አሥራ አምስት ዓመት በወንጌላዊው በዮሐንስ ቤት ከኖረች በኋላ በ64 ዓመቷ ጥር 21 ቀን ዐርፋለች፡፡
በሐዋርያትም ውዳሴ፣ ዝማሬና ማኅሌት ነሐሴ 14 ቀን ከተቀበረች በኋላ በነሐሴ 16 ተነሥታ በይባቤ መላእክት ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡ ቅዱስ ያሬድ በመዝሙሩ €œተለዐለት እምድር ወበህየ ነበረት ዘምስለ ወልዳ፣ በየማነ አብ ወመንፈስ ቅዱስ እመቤታችን ድንግል ማርያም ከምድር ወደ ሰማይ ዐረገች፡፡ በሰማይም ከልጅዋ ጋር በአብና በመንፈስ ቅዱስ ቀኝ ተቀመጠች€ እና ከሺሕ ዓመትም በፊት አባቷ ዳዊት €œበወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች€ /መዝ. 44፡9/ እንዳለ፡፡
ፍልሰት የሚለው ቃል የእመቤታችን ሥጋ ከጌቴሴማኒ ወደ ገነት መፍለሱን ኋላም በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ለማመልከት የሚነገር ነው፡፡ /ወላዲተ አምላክ በኢትዮጵያ – 68/
ለሐዋርያት የእመቤታችን የዕረፍትና የዕርገት ምሥጢር የተገለጠላቸው በሱባዔ ነው፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ በየዓመቱ ጾመ ፍልሰታ ወይም የሐዋርያት ሱባዔ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ይታሰባል፣የቻሉ ርቀው ስባዔ ገብተው፣ያልቻሉ በአጥቢያቸው የውዳሴዋና የቅዳሴዋን ትርጉም ይሰማሉ፣በሰዓታቱና በቅዳሴው መርሀ ግብራት ይሳተፋሉ፡፡በእመቤታችን አማላጅነት በልጇ ቸርነት በምድር ሳሉ በሃይማኖት ጸንተው ለመኖር ኋላም ለመንግሰቱ እንዲያበቃቸው ድጅ ይጠናሉ፡፡
የሱባዔ ዓይነቶች
የግል ሱባዔ/ዝግ ሱባዔ/
የግል ሱባዔ አንድ ሰው ብቻውን ሆኖ በቤትና በአመቺ ቦታ የሚይዘው ማንም ሰው ሳያየው በግሉ የጸሎት በኣቱን ዘግቶ በሰቂለ ኅሊና ሆኖ ፈጣሪው ብቻ እንዲያየው እንዲሰማው በኅቡዕ የሚፈጽመው ሱባዔ ነው፡፡ ማቴ.6፡5-13፡፡ በዚህ ዓይነት መልክ አንድ ሰው ሱባዔ ሲገባ ዘጋ ይባላል፡፡ ዝግ ሱባዔ የያዘ ሰው የሚያስፈልገውን ነገር ይዞ ወደ በኣቱ ከተከተተ በኋላ ሱባዔው እስኪፈጸም ድረስ ከሰው አይገናኝም፡፡ መዝ. 101-6-7፡፡
የማኅበር ሱባዔ
የማኅበር ሱባዔ የሚባለው ካህናት፣ ምእመናን ወንዶችና ሴቶች፣ ሽማግሌዎችና ወጣቶች በአንድ ሆነው በቤተ ክርስቲያንና አመቺ በሆኑ ቦታዎች ሁሉ ተሰብስበው የሚገቡት ሱባዔ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን የነበሩ ምእመናን ወደ እግዚአብሔር በመሄድ ይጸልዩ ነበር፡፡ 1ኛ ሳሙ.1፡9፤ መዝ.121፡1፤ ሉቃ.18፡10-14፡፡
በሐዲስ ኪዳንም የሐዋርያት ተከታዮች የኾኑ መነኮሳት፣ ካህናትና ምእመናን በገዳማት፣ በአድባራት፣ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች፣ የጽዋ ማኅበርተኞች ስለ ማኅበራቸው ጥንካሬና ከማኅበርተኞቹ መካከል አንዱ ችግር ሲገጥመው የማኅበር ሱባኤ ይያዛል፡፡.
የዐዋጅ ሱባዔ
የዐዋጅ ሱባዔ በአገር ላይ ድንገተኛ አደጋ፣ አባር ቸነፈርና ጦርነት ሲከሰት እንዲሁም ለማኅበረ ምእመናን አስጊ የሆነ መቅሰፍት ሲከሰት፣ እግዚአብሔር መዓቱን በምሕረት ቁጣውን በትዕግሥት እንዲመልስ የሚያዝ የሱባዔ ዓይነት ነው፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ሱባዔ የነነዌ ሰዎችና በፋርስ በስደት ይኖር የነበረ እስራኤላውያን ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የነነዌ ሰዎች የዮናስን ስብከት ሰምተው ከሊቅ እስከ ደቂቅ ለሦስት ቀን ከመብል ከመጠጥ ተከልክለው በመጾም በመጸለይ እግዚአብሔር መዓቱን በምሕረት ቁጣውን በትዕግሥት እንዲመልስ አድርገዋል፡፡ ሌላው በፋርስ በስደት ይኖር የነበረ አይሁድ በአስቴር ትእዛዝ የያዙት ሱባዔ ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚያን ዘመን አርጤክስስ አይሁድ በያሉበት እንዲገደሉ በማዘዙ ከዚህ የጅምላ ጭፍጨፋ ለመዳን አይሁድ በዐዋጅ ሱባዔ ገብተዋል፡፡ አስቴር ገብታ ንጉሡን ስታናግረው ሌላው ሕዝብ በውጭ ዐዋጅ ዐውጀው ሱባዔ ገብተው ፈጣሪያቸውን ተማፅነዋል፡፡ አስቴር 4፡16 – 28፡፡
በአገራችንም ይህን የመሰለ የዐዋጅ ሱባዔ በዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ተደርጓል፡፡ ፋሽስት ጣልያን አገራችንን በመውረር ኢትዮጵያን ቅኝ ተገዥ ለማድረግ ድንበሯን አልፎ በመጣበት ወቅት ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ፡-ጉልበት ያለህ በጉልበትህ ጉልበት የሌለህ በጸሎትህ ርዳኝ በማለት የዐዋጅ ሱባዔ መያዛቸው ይነገራል፡፡ በዚህም መሠረት በየገዳማቱ ምሕላ ተይዟል፤ ንጉሡም ታቦተ ጊዮርጊስን ይዘው ዓለምን እጅግ ያስደነቀ ጥቁሮችን ለነጻነታቸው እንዲነሣሱ የሚያስችል ፋና ወጊ የሆነ ድል አግኝተው አገራችንን ለቅኝ ግዛት ያሰበውን ፋሽስት ጣልያንን ማሸነፋቸው በከፍተኛ ስሜት የምናስታውሰው ነው፡፡
ቅድመ ዝግጅት
ሱባዔ መግባት የሚፈልግ ምእመን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ያለምንም ዝግጅት ሱባዔ መግባት ለፈተና ያጋልጣል፡፡ ስለዚህ ቅድመ ሱባዔ /ሱባዔ ከመግባት አስቀድሞ/፣ ጊዜ ሱባዔ/ በሱባዔ ጊዜና ድኅረ ሱባዔ /ከሱባዔ በኋላ/ ዝግጅት አስፈላጊ ነው፡፡
ቅድመ ሱባዔ /ሱባዔ ከመግባት አስቀድሞ/
በመጀመሪያ ሱባዔ የምንገባበትን ምክንያት ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ አንድ ሰው ሱባዔ የሚገባበትን ዓላማ ለይቶ ካስቀመጠ ከሱባዔ በኋላ የሚጠበቀውን ነገር ማግኘት አለማግኘቱን ይረዳል፡፡ ይህ ሳይሆን ሱባኤ ቢገባ ከሱባኤው በኋላ የጠየቀው ነገር ስለሌለ ትርጉም ያጣል፡፡ ስለዚህ ሱባዔ ከመግባታችን በፊት ለምን ሱባኤ ለመግባት እንዳሰብን ለይተን ማወቅ ይኖርብናል፡፡
ሱባዔ ለመግባት የወሰንበትን ምክንያት ከለየን በኋላ ምክንያታችንን ይዘን የንስሐ አባታችንን ማማከር ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም በምክረ ካህን መጓዝ መጀመር ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር በአባትነታቸውና በሕይወት ልምዳቸው ምን ማድረግ እንደሚገባን ምክር ለማግኘት እገዛ ያደርግልናል፡፡ ቅድመ ሱባኤ ከንስሐ አባት ጋር መመካከር ተገቢ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው በሱባዔ ወቅት የተለያዩ ፈተናዎች ቢያጋጥሙት የተሰጠውን ምክር በመጠቀም ፈተናውን ለመቋቋም ይችላል፡፡ እንዲሁም የንስሐ አባቱ በሱባዔ ወቅት በጸሎት እንዲያስቡት መማከር የራሱ የሆነ ድርሻ አለው፡፡
ሱባዔ ለመግባት ስናስብ ለምን ያህል ቀናት መቆየት እንዳለብን መወሰን ያስፈልጋል፡፡ ሱባዔ ከዚህ እስከዚህ እቆያለሁ ብለን ዕቅድ የምንይዝበት ነው፡፡ እንደ አቅማችንና እንደ ችሎታችን ከዚህ ቀን እስከዚህ ብለን በመወሰን ሱባዔ መግባት ተገቢ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ፡- ምንም ዓይነት ልምድ ሳይኖረው አንድ ሰው በዋሻ እዘጋለሁ ቢል ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል፡፡ ምክንያቱም በሱባዔ ወቅት ፈተና ስለሚበዛ የሚመጣበትን ፈተና መቋቋም ባለመቻል ሱባዔው ሊቋረጥ ይችላል፡፡ ስለዚህ ቅድመ ሱባዔ ዐቅምንና ችሎታን አገናዝቦ መወሰን ተገቢ ነው፡፡
ሌላው ቅድመ ሱባዔ ለሱባዔ ተስማሚ የሆነ ወቅትና ቦታ መምረጥ ተገቢ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን በአብዛኛው ሱባዔ የሚገባው አጽዋማትን ተከትሎ ነው፡፡ ስለዚህ ሱባዔ የምንገባበት ወቅት የጾም ወቅት መሆን አለመሆኑን መለየት ያስፈልጋል፡፡ በአጽዋማት ወቅት የሚያዝ ሱባዔ ለተሐራሚ ጠቀሜታው እጅግ የጐላ ነው፡፡ ምክንያቱም በአጽዋማት ወቅት ብዙ አባቶች ሱባዔ ስለሚይዙ ከአባቶች ጸሎት ጋር ልመናችንና ጸሎታችን ሊያርግ ይችላል፡፡ ስለዚህ ወቅትን ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
እዚህ ላይ ከወርኃ አጽዋማት ውጭ ሱባዔ አይያዝም የሚል አቋም ለመያዝ አይደለም፡፡ አንድ ሰው ፈተና ከአጋጠመው በማንኛውም ጊዜ ሱባዔ ሊገባ እንደሚችል እዚህ ላይ ለመጠቆም እንወዳለን፡፡ ከዚህም ባሻገር ሱባዔ የምንይዝበትን ቦታ መምረጥ አለብን፡፡ ለሱባዔ የምንመርጣቸው ቦታዎች ለፈተና የሚያጋልጡ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ይኸውም ሱባዔ ከተገባ በኋላ ኅሊናችን እንዳይበተን እገዛ ያደርግ ልናል፡፡ ጫጫታና ግርግር የሚበዛበት ቦታ በሰቂለ ኅሊና ለመጸለይ አያመችም፡፡ ስለዚህ ሱባዔ የምንይዝባቸው ቦታዎች ከከተማ ራቅ ያሉ ገዳማትና አድባራት ተመራጭ ናቸው፡፡
ጊዜ ሱባዔ /በሱባዔ ጊዜ/
በጸሎት ሰዓት ዓምድና ግድግዳ ሳይደገፉ መቋሚያ ሳይዙ በሁለት እግር ቀጥ ብሎ በመቆም መጸለይ ይኖርብናል፡፡ እንዲሁም ፊትን ወደ ምሥራቅ መልሶ መቆም ወዲያና ወዲህ ወደ ግራ ወደ ቀኝ አለመዟዟር በሰፊሐ እድ በሰቂለ ኅሊና ኾኖ መጸለይ ይገባል፡፡ መዝ.5፡3፤ መዝ.133፡2፤ ዮሐ.11፡41፡፡
በመጨረሻም ሱባዔ የገባ ሰው ሱባዔውን ሳይጨርስ ወይም ሱባዔውን አቋርጦ ከማንም ሰው ጋር ፈጽሞ መገናኘት የለበትም፡፡
ድኅረ ሱባዔ /ከሱባዔ በኋላ/
ለቀረበ ተማኅፅኖ እግዚአብሔር የሚያደርግልንን ነገር መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ እግዚአብሔር ላቀረብንለት ምልጃና ጸሎት እንደ ልባችን መሻት እንደ እርሱ ቸርነት እርሱ በወደደ ጊዜ ያደርግልናል፡፡ ከሱባዔ በኋላ መጀመሪያ የምናገኘው የህሊና ሰላምን ነው፡፡ ይህ ትልቅ የአምላክ ስጦታ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ሱባዔ ገብተን ያሰብነውን ካላገኘን ዳግመኛ ተዘጋጅተን እስከ መጨረሻው ሰዓት መማፀን መጽናት ይኖርብናል፡፡

ሥራህን ሥራ (በአቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ)

ጌታ ለእያንዳንዱ ሰው ሥራ ሰጥቶታል ያንን መስራት የእሱ ፈንታ ነዉ። ቢቻለዉ እሱን ማገድ የዲያብሎስ ሥራ ነዉ። በእርግጥ ሥራዉን እግዚአብሔር እንደሰጠህ ያህል ሰይጣን ሊያግድህ ይሞክራል። ሌላ ነገር በበለጠ ደስ የሚያሰኝ ሊያቀርብልህ ይጥራል። በዓለማዊ ተስፋዎች ያባብልሃል የሐሜት ጎርፍ ያስወርድብሃል። ደራሲያን ኦንዲጠይቁህ እጅግ ስመ ጥሩ ሰዎችም በክፋ እንዲናገሩብህ ይጠቀምባቸዋል። ጲላጦስ፥ሄሮድስ፥ሀናንያ፥ቀያፋ ሁሉም በአንተ ላይ ያድማሉ . . . አንተ ግን በፀና ውሳኔ በማያወላውል ቅናት በመጨረሻ ላደርገው የሰጠኽኝን ስራ ፈፀምኩ ሃይማኖቴንም ጠበቅሁ ለማለት እስክትችል ድረስ የሕይወትህን ዓላማ እና የተፈጠርክበትንም ግብ ተከተል።
አባ ጎርጎርዮስ ካልዕ
የሸዋ ሊቀ ጳጳስ ፩፱፫፪፡፩፱፰፪ ዓ.ም.
               በዮሐንስ አፈወርቅ
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መሠረቷኗ ጉልላቷ ክርስቶስ በመሆኑ የሰላም ደጅ ናት፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለተሰሎንቄ በጻፈው መልእክቱ “የሰላምም ጌታ ራሱ በሁሉ መንገድ ዘወትር ሰላምን ይስጣችሁ፡፡ ጌታ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፡፡” (2ኛ ተሰሎ 3፡16) እንዳለ በክርስቶስ ሰላም እየተጠበቀች አንድነቷ ላይ የሚያጋጥሟትን ፈተናዎች ሁሉ እየተቋቋመች አገልግሎቷን በማስፋፋት ምእመናንን ትጠብቃለች፡፡ አባቶችም ከቤተ ክርስቲያን የተቀበሉትን አደራ ተግተው በመጠበቅ መንጋውን በክርስቶስ ሰላም ማጽናት ይኖርባቸዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቁ ዘንድ ለመንጋውና ለራሳቸውም መጠበቅ ጥንቃቄ ያደርጉ ዘንድ የእግዚአብሔር ቃል ያስተምረናል፡፡ «በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ፣ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጐ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ» ሐዋ 20፡28
በመሆኑም የቤተ ክርስቲያን ጭንቀቷ ለጊዜያዊውና ለሚያልፈው ሳይሆን ለዘላለሙ፣ ለምድራዊው ሳይሆን ለሰማያዊው ሕይወት በመሆኑ፣ ዓለሙ ከሚከፋፈልበት የዘር፣ የጐሳ፣ የቋንቋና የርዕዮተ ዓለም አመለካከት ልዩነቶች የራቀች መሆን ይጠበቅባታል፡፡ የመንፈስ ልጆቿን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ወልዳ ከማይጠፋ ዘር በክርስቶስ ሥጋና ደም አንድ አድርጋ የምትመራ ለአንድና ለማያልፍ የእግዚአብሔር መንግሥት የምትሠራ ነፍሳትንም ለዚህ ክብር የምታዘጋጅ ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን ጉልላቷ አንድ በመሆኑ፣ ልጆቿ ሁሉ በእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ የአንድ አካል ብልቶች እንዲሆኑ ትሠራለች፡፡ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮች ሁሉ፣ ትእዛዛተ እግዚአብሔርን የሚፃረሩ በመሆናቸው፤ ለጥላቻዎችና መለያየቶች መንስኤ የሆኑ ነገሮችን አጥርቶ ማየትና መፍትሔ ለመስጠት መሄድ ሕገ እግዚአብሔርን መፈጸም ነው፡፡
ጥላቻዎችና መለያየቶች ሰላመ ቤተክርስቲያንንና ሕዝበ እግዚአብሔርን የሚያውኩ በመሆናቸው፣ በእነዚህ አትራፊ የሚሆነው፣ ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ብቻ እንጂ፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንና ተከታዮቿ የሆኑት ሕዝበ እግዚአብሔር አይደሉም፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዓለሙ የሚለያይባቸውን ነገሮች የምታወግዝ እንጂ፣ አካሏን ለሚለያይና ፍቅርን ለሚያደበዝዙ ክፍተቶች አሳልፋ መተው የለባትም፡፡ እንኳን የራስን አካል ቀርቶ ቃሉ ጠላትንም መውደድ እንዲገባን ያስተምረናል፤ “እኔ ግን እላችኋለሁ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ የሚረግሙአችሁን መርቁ ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ ይላልና—“ (ማቴ 5፡44-45) ክርስቲያኖች ሁሉ እውነተኛ ጨው ሆነን ዓለሙን ማጣፈጥ ሲገባን ይህን ቸል ብለን መንጋውን ለዓለሙ ክፉ ሐሳብ፤ መለያየትና ለዘረኝነት መራራ ፍሬ አሳልፈን እንዳንሰጥ መጠንቀቅ ይገባናል፡፡
ቅዱሳን ሐዋርያት ለዓለሙ ጨው ሆነው የወንጌልን ፋና ያበሩት፣ በአንድ ልብ ሆነው በጸሎትና በጾም በመትጋታቸው የመንፈስ ፀጋን በመጎናጸፋቸው ነው እንጂ፤ እርስ በርሳቸው በመለያየት አይይደለም፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፡- በአጥቢያዎች፣ በወረዳና በአህጉረ ስብከት የተደራጀች ስትሆን፤ እነዚህ መዋቅሮቿ፣ ጉልላቷና መሠረቷ የሆነውን የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትእዛዛት፣ መርሓቸው አድርገው የሚሄዱ እንጂ «ከእርሱም የተነሣ አካል ሁሉ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ፣ በተሰጠለት በጅማት ሁሉ እየተጋጠመና እያተያያዘ፣ ራሱን በፍቅር ለማነፅ አካሉን ያሳድጋል» ኤፌ 4፡16 ተብሎ የተጻፈውን በመቃረን፣ በየራሣቸው የሚመሩ፣ የማይነጋገሩና የማይተጋገዙ፣ አንዱ ለሌላኛው ግብኣት የማይሆኑ ብልቶች ሆነው በየግላቸው የሚጓዙ አይደሉም፡፡
ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚያርቁ ምክንያቶችና ክስተቶች፣ የክርስቶስ አካል በሆነችው የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሉዓላዊነት ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ስለሆኑ፤ እነዚህን ምክንያቶችና ሁኔታዎች እያንዳንዳችን ትኩረት ሰጥተን መመርመርና ማየት ይገባናል፡፡ በመሆኑም ፈራጅ በመሆን ብቻ ወይም አጋጣሚውን ለየግል ፍላጐታችን መጠቀሚያ በማድረግ፡- መለያየትንና ጥላቻን የምናበረታታና የምናሣድግ፣ በአጠቃላይም ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የማይጠቅሙ ነገሮች እድል እንዲያገኙና ተደብቀው እንዲያድጉ፣ በቸልተኝነት ቀዳዳ የምንፈጥር እንዳንሆን መጠንቀቅ ይገባናል፡፡
ዓለሙ በራሱ ፍልስፍናና ምድራዊ ጥበብ፣ ሕግጋተ እግዚአብሔርን ባለመጠበቅ፣ የቅድስት ቤተክርስቲያንን ህልውና ለራሱ በሚመቸውና በሚጠቅመው መንገድ እንዲሆንለት ይሠራል፡፡ ጥበብ ምድራዊን መርሑ አድርጐ የሚሄድ ሰው ወይም አካል፡- የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሉዓላዊነት ዕውቅና ሰጥቶ ከመጠበቅ ይልቅ፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለእርሱ ተገዢና ዓላማ ማስፈጸሚያ እንድትሆንለት ይሻል፡፡ በዚህ ጊዜም የቅድስት ቤተክርስቲያን አባቶች በጥበብ ምድራዊ አመለካከት የሚገጥማቸውን ፈተና በጸሎት ተግተው፣ እየተመካከሩ ድል ያደርጉታል እንጂ፣ ፈተናው ከራሳቸው አልፎ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አንድነት፣ ህልውናና አገልግሎት እንዲገዳደር ዕድልና ቀዳዳ የሚፈጥሩለት አይሆኑም፡፡
የቤተ ክርስቲያንን አድነት ለማስጠበቅ አባቶች፡- ፈቃድ፣ አቅጣጫ፣ ኃይልና ጥበብ የሚጠይቁት፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን መሪ ከሆነው ከመንፈስ ቅዱስ እስከሆነ ድረስ፤ የዓለሙን ፍላጐትና ሐሳብ የሚከተል፣ በእርሱም ተጠልፎ የሚወድቅ አይደለም፡፡ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባቶች ሕይወትና ሥራ ሙሉ ለሙሉ የእግዚአብሔርን ክብርና የቤተክርስቲያንን ደኅንነት ቅድሚያ ሰጥቶ ለማረጋገጥ የቆመና ቁርጠኝነት ያለው ሲሆን፤ የዓለሙ ፍላጐት፣ ተፅዕኖ ሊያሳርፍበት አይገባም፡፡
የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት፡- በጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሠረትነት ላይ የታነፀ፣ መንገዱም፡- ግልፅ፣ አንድና የቀና እንጂ፤ ለግል አመለካከትና ፍላጐት ተገዢ የሚይሆን፤ በፈለግን ጊዜ የምንሄድበት? ባልፈለግን ጊዜ ደግሞ መዝጋትም ሆነ መገደብ የምንችለው አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ «ማንም እራሱን አያታል፤ ከእናንተ ማንም በዚች ዓለም ጥበበኛ የሆነ ቢመስለው፣ ጥበበኛ ይሆን ዘንድ ሞኝ ይሁን» 1ቆ 3፡18 ተብሎ እንደተጻፈው የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ህልውና የሚፈታተኑ ነገሮችና ሐሳቦች በሚፈጠሩበት ጊዜ፣ በመግባባትና በመተማመን ለመፍታት መሄድ ይገባል እንጂ፣ በራሳችን ጥበብ ጌታችን በሥጋና በደሙ ለመሠረታት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሰላም መጠናከር አስተዋጽኦ ለማያደርጉ ሁኔታዎች አሳልፈን የምንሰጥ እንዳንሆን መጠንቀቅ ይገባናል፡፡
አባቶች የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሰላም፣ ሉዓላዊነትና አንድነት ጠንክረው የሚያስከብሩ በሚሆኑበት ጊዜ፣ ምእመናን ለፈተና ባለመጋለጥ ጸንተው በአጸዷ ውስጥ ለመኖር ያግዛቸዋል፡፡ በዓለሙ ያሉ ሰዎችም፣ ለአባቶች ክብር እንዲሰጡ ያደርጋቸዋል፡፡ አባቶች ሲናገሩ ተደማጭነትን፣ ሲመክሩ ደግሞ ተሰሚነትን ከሕዝቡ ሁሉ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል፡፡ «የራሷ ሲያርባት የሰው ታማስል» የሚለው አባባል ሳይጠቀስባቸው፣ ከራሳቸው በመትረፍ፣ በሀገሪቱ ችግሮች አፈታት ላይ ከፍ ያለ ቦታና ተፈላጊነት ያላቸው እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፤ ክብርና ሞገስም ያስገኝላቸዋል፡፡ ብዙዎችን በፍቅር መሸምገል የሚገባው እርሱ ለሽምግልና አስቸጋሪ ሊሆን አይገባም፡፡ ክርስትና በተግባር የሚታይ ሕይወት ነውና፡፡
ቤተ ክርስቲያን አንዲት ሆና እያለች «የውጪ እና የሀገር ውስጡ ሲኖዶስ» በሚል ሐዋርያዊ አገልግሎቷና የምእመናን አስተዳደሯ እርስ በርሳቸው በማይመካከሩና አንዱ ለሌላኛው ዕውቅና በማይሰጣጡ አካላት ለመምራት ሲኬድ የቆየ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎትና በምእመናን ሕይወት ላይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሮ ቆይቷል፡፡ በመሆኑም እያንዳንዳችን ለችግሩ መፈጠር በቀጥታ ምክንያት ላንሆን ብንችል እንኳ፤ ከክስተቱ በኋላ ከትእዛዛተ እግዚአብሔርና ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አንጻር ተመልክተን ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ ለመስጠት በሚገባው መጠን ያህል ያልሄድን፤ ለቅድስት ቤተክርስቲያን አንድነት ቅድሚያ ባለመስጠት በቸልተኝነት ሁኔታው እየተባባሰ እንዲሄድ ያደረግን፤ ወይም ችግሩን መንፈሳዊ ከሆኑ አቅጣጫዎች ይልቅ፣ ዓለማዊና ግላዊ ከሆኑ ነገሮች አንፃር ስንመለከተው የቆየን ከሆነ፤ ለተፈጠረው ችግር የሚመለከተን ሁሉ ከሚጠበቅብን አንፃር፣ ባለድርሻዎች ናችሁ ብንባል፤ ቢያንሰን እንጂ የሚበዛብን አይሆንም፡፡
በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር መለያየት ምክንያት በውጭ ያሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አድባራት፡- በሀገር ውስጥ ባለው ሲኖዶስ የሚመሩ፣ በውጭ ሀገር የተቋቋመውን ሲኖዶስ እንደግፋለን በሚሉና ከሁለቱም ሳይሆኑ ገለልተኛ ነን በሚሉ ሦስት ቡድኖች ተከፋፍለው የሚገኙ ሆነዋል፡፡ የዚህ ሁሉ ክፍፍል መንስኤው፣ የተፈጠረውን ችግር በወቅቱ ሃይማኖታዊ በሆነ መንገድ ፈቶ መሄድ ባለመቻሉ፣ ማለትም የአንድነት አለመኖር ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ግልጽና የታወቀ ነውና፣ በመንፈሳዊነት ማሸነፍና መሸናነፍ ባለመቻሉ፣ ዓለማዊ የሆኑ ፍላጐቶችና ተፅዕኖዎች አይለውና ተሰሚነት አግኝተው በመቆየታቸው ነው፡፡ አሁንም ይህ መከፋፈል ካልተገታ፣ አሁን ካለው እያደገ በመሄድ፣ ብዙ ውስብስብና አስፈላጊ ያልሆኑ ሁኔታዎችን ሊፈጥር ይችላል፡፡
የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባቶችና ምእመናን ዘመኑን የዋጁ ካልሆኑ፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ጉዳዮች፣ ዓለማዊ የሆኑ ፍላጐቶችና ተፅዕኖዎች ምን ጊዜም መፈታተናቸው የማይቀር ነው፡፡ በዚህ ጊዜም፡- ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰላም፣ አንድነትና ህልውና ጠቃሚ የሆኑ ነገሮችን እየወሰድንና እየተባበርን የቅድስት ቤተክርስቲያን አንድነት የተጠናከረ፣ አገልግሎቷ የሰመረ፣ ምእመኖቿ በመንፈስ ቅዱስ መሪነትና በማንኛውም አቅም የተሰናሰሉና የጠነከሩ፣ ተስፋ መንግሥተ ሰማያት ያላቸው እንዲሆኑ፣ ዕንቅፋቶችን ሁሉ ማስወገድ እንደየድርሻችን የሁላችንም ተግባር ነው፡፡ ይህንን መፈጸም አባቶችና ምእመናን ከራሳቸው በማለፍ ለሀገሪቱ ዕድገትና ሰላም ድርሻቸው የላቀ እንዲሆን፤ ባጠቃላይም የሀገርን ችግር በመፍታቱ በኩል የሚኖራቸው ተፈላጊነትና ድርሻ ከፍ ያለ ደረጃ እንዲኖረው ያደርጋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በውጪ ሀገር ካሉ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋር መግባባት እንዲኖር በተለያዩ ጊዜያት የዕርቀ ሰላም ልዑካንን በመላክ፣ በውጭ ሀገር ያሉ አባቶችም ለድርድር ፈቃደኛ በመሆን፣ ውይይቶች እየተጀመሩ እልባት ላይ ሳይደረስ፣ እንዲሁ ይቀሩ የነበረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በቅርቡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምት 2ዐ1ዐ ዓ.ም. ባደረገው መደበኛ ጉባኤው፣ አጀንዳ ቀርጾ ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች መካከል፡- በውጭ ሀገር ካሉ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋር ተጀምሮ የነበረው የዕርቀ ሰላም ድርድር ቀጥሎ መፍትሔ እንዲያገኝ የሚለው አንዱ ነው፡፡ ነገሩ ሁለት ዐሥርት ዓመታትን ያሳለፈ ስለሆነ፣ እንደ ጉዳዩ አሳሳቢነት በፍጥነት እየተሄደበት ነበር ባይባልም፣ ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ በቋሚ ሲኖዶሱ አስፈላጊው ዝግጅት ሲደረግበት ከቆየ በኋላ፣ በአሁኑ ሰዓት ለሕዝበ ክርስቲያኑና ለሚመለከታቸው አካላት ግልጽ ተደርጐ፣ በሁለቱም ወገን ተወያይ የሆኑ አባቶች እና የዕርቀ ሰላም ኮሚቴው ለዝግጅቱ ደፋ ቀና በማለት ላይ ይገኛሉ፡፡
የምንስማማውና ዕርቅ የምናደርገው፡- ያስቀየምንና የተቀየምን፣ የበደልንና የተበደልን፣ ይቅር ልንልና ልንባባል ነው፡፡ በአባቶች መካከል ለተፈጠረው አለመግባባት ዕርቀ ሰላም የምናደርገው በሐዋርያት ሥራ 2ዐ፡28 እንደተገለጸው፣ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአባቶች የሰጠው የኖላዊነት ተግባር በአግባቡ ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡ በዚህም፡- ምእመናን ወደ ለመለመው መስክ ሊመራቸው የሚገባ ጠባቂ በማጣት ለነጣቂ ተኩላ ሳይጋለጡ፤ በአንድ በረት ውስጥ ተጠብቀው፣ የመንግሥተ ሰማያት ወራሾች ይሆኑ ዘንድ ለማስቻል፣ ዕንቅፋት የሚሆኑ ነገሮችን ጊዜና ፋታ ሳይሰጡ ማስወገድና ማስተካከል የትጉህ እረኛ ተግባር ነው፡፡
ከዚህ አኳያም፡- የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባቶች የዓለሙን ክብርና ጥቅም ንቀው የሚተጉ ናቸውና፤ በድርድራቸው ላይ የሚያስቀድሙት የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ፍላጐትና ህልውና ስለሆነ፤ መግባባት የማይችሉባቸው ነጥቦች ይኖራሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ አባቶች ተለያይተው በመቆየታቸው አንዳቸው በሌላኛው ላይ የሚያነሷቸው ነጥቦች ሊኖሩ ቢችሉ እንኳ፣ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገትና ህልውና ተፃራሪና ድብቅ የሆነ ነገር በመካከላቸው የሌለ እስከሆነ ድረስ፣ ይቅር ለመባባል በግንባር ቀደምትነት መቀመጥ ከሚገባቸው የጋራ መርሖዎች (የማስማሚያ ነጥቦች) በተጨማሪ፡- በቀጣይ መስተካከልና መታረም ያለባቸውን ቀሪ ዋና ዋና ነገሮች ርእሰ ጉዳይ አስቀድሞ ለይቶ በጥቅሉ በመያዝ፣ ከይቅር መባባሉ በኋላ በአደራዳሪዎች አማካኝነት በዝርዝር በመነጋገር እየፈቱ ለመሄድ፣ ከወዲሁ ሥርዓት ማበጀት አጋዥነት ያለው ነው፡፡ ርእሰ ጉዳያቸው በቅድሚያ ተመዝግቦ በቀጣይነት ለሚነሡ ነጥቦች ሁሉ፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሕግና ሥርዓት፣ ገዢነትና መሪነት ያለው በመሆኑ፤የዕርቀ ሰላሙ ሂደት የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያልሆነ፣ የግልም ሆነ የቡድን ፍላጐት፣ አቋምና አካሔድ ጥላ ሊያጠላበት የሚችል አይደለም፡፡ዋናው ነገርም ዕርቀ ሰላሙን አጽንቶ ለመሄድ፣ በልዩነቱ ጊዜ ውስጥ የተፈጠሩ መታረም፣መታየትና የጋራ መደረግ ያለባቸውን ሁኔታዎችና አሠራሮች፣ከሁሉም ወገን ሰብስቦ፣በአደራዳሪ ሽማግሌዎች አማካኝነት ቅቡልነት ያለው አቅጣጫ እንዲያዝባቸው ማድረግ ነው፡፡
ስለ ዕርቀ ሰላሙ አስፈላጊነት፣ የአፈጻጸም ቅደም ተከተል፣ ስለ ምእመናንና የካህናት ድርሻ፣ በደንብ ታስቦበት በተዘጋጀ ሁኔታ፣ በየጊዜው በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ሂደቱ ስለሚገኝበት ደረጃ መግለጫዎችንና መረጃዎችን መስጠት፣ የዕርቀ ሰላም ኮሚቴው ተግባር ለውጤቱም አጋዥነት ያለው ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሁለቱም ወገን ለመነጋገርና በመሃል ላይ ሆኖ ለማነጋገር የምንቀርብ አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችም፣ ከዚህ በፊት ተጀምረው የነበሩ ውይይቶች ውጤት ያላመጡት ለምንድን ነው? በሁለቱም ወገኖች አቀራረብ ላይ የነበረው ጠንካራና ደካማ ጐን ምን ነበር? አሁን በቀጣይ ለሚደረገው ምክክር፣ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት መጠናከር ሲባል በእኔ/በእኛ በኩል፣ ተስተካክሎ መቅረብ የሚገባው አቋም ምንድን ነው? ብሎ በተለያዩ የአማራጭ አቅጣጫዎች አስቀድሞ በግልና በቡድን ደረጃ ማየት፣ መዘጋጀትና መሥራት አስፈላጊ ነው፡፡
ሰላመ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፣ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ሲል ትልቅ ዋጋ የከፈለበት ሀብተ ክርስትናችን ስለሆነ፣ የምናጸናው አባቶችና ምእመናን ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ህልውና በእውነት በመትጋት በአንድነት ሆነን እንደየድርሻችን አገልግሎቷን ስንፈጽም ነውና፤ ዕርቀ ሰላሙ ጊዜ የሚሰጠው አይደለም፡፡ በተለይም መለያየትን መግቢያ ቀዳዳው በማድረግ ጠላት ዲያብሎስ የራሱን ተልዕኮ ለመፈጸምና ለማስፈጸም ወደ ኋላ አይልምና፤ ዕርቀ ሰላሙን ዳር ለማድረስ ባለፉት ዓመታት ውጤታማ መሆን ባይቻልም፤ ከሚመጣው 2ዐ11 ዓ.ም. መቅደም መቻል ብልህነት ነው፡፡ ስለሆነም ኅብረታችን የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ከሚያፋጥኑ ጋር እንጂ፤ በውስጧ ሆነው ከሚቦረቡሯት የተሐድሶ መናፍቃን ጋር አይደለምና፤ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር፣ ሐዋርያዊ አገልግሎቷን፣ አንድነቷንና ዐቅሟን ለማጠናከር የሚረዱ ነገሮችን ለመፈጸም፣ ኃይለ እግዚአብሔርን አጋዥ አድርጐ መንቀሳቀስ ዘመኑን መዋጀት ነው፡፡
የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነትና ዐቅም እንዲጠናከር በተቻለው መጠን እየሠራ ያለው ማኅበረ ቅዱሳንም፣ በአባቶች መካከል ተፈጥሮ መፍትሔ ሳይሰጠው የቆየው መለያየት፣ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አይጠቅምም በማለት አቋሙን ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ ለምሳሌም በሐመር መጽሔት ላይ ብቻ ካስተላለፋቸው መልእክቶች መካከል፣ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ከወጡት ላይ የተወሰኑትን ብንመለከት፡- በ1999 ዓ.ም. ሐመር 15ኛ ዓመት ቁጥር 1 የጥርና የካቲት ዕትም ላይ፣ ከቅርብ ዓመታት በፊት በ2ዐዐ5 ዓ.ም. ላይ ደግሞ በሐመር 2ዐኛ ዓመት ቁጥር 5 መስከረም ወር ዕትም ላይ «ለቤተ ክርስቲያናችን አንድነት፣ ዕርቅና ሰላም መሠረት ናቸው» በሚል ርእስ እንዲሁም በሐመር 2ዐኛ ዓመት ቁጥር 6 የጥቅምት ወር ዕትም ላይ፡- ወቅቱ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው ምክንያት በምትካቸው ሌላ ፓትርያርክ ለመሾም ጥረት እየተደረገበት የነበረ ጊዜ በመሆኑ «ከሁሉም ነገር በፊት ዕርቀ ሰላም፣ ማሠራቱ የተረጋገጠለት ሕገ ቤተክርስቲያንና የምርጫ መመሪያ ያስፈልጋል» በማለት መልእክት አስተላልፏል፡፡ አሁንም ቢሆን ማኅበሩ ዕርቀ ሰላሙ የተሳካ እንዲሆን ጽኑ የሆነ ፍላጐት ያለው ስለሆነ፤ የሚችለውን ድጋፍ ለማድረግና በአባቶች የሚታዘዘውን በዐቅሙ ለመፈጸም ዝግጁ መሆኑን ይገልጻል፡፡
በአጠቃላይም፡-
1. የዕርቀ ሰላሙ ድርድር የሚጀመረው በጸሎትና በአባቶች ቡራኬ በመሆኑ፤ ሕዝበ ክርስቲያኑም መለያየቱ ዓመታትን በመውሰዱ ላይ እያዘነ ስለሆነ፤ የሚታረቁና የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው ተብሎ በተጻፈው መሠረት እኛ ፈቃደኞችና ቁርጠኞች እስከሆን ድረስ፣ ፈቃደ እግዚአብሔር የማይለየን ስለሆነ፣ ዕርቀ ሰላሙ ይሳካል ብሎ በሙሉ ልብ መጀመር፡፡
2. ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለሀገሪቱ ሰላምና አንድነት ብዙ እንዳላበረከተች ሁሉ፤ አጀንዳ ሁኖ የሚገኘውን ይህን የራሷን ጉዳይ ሳትፈታ መቆየቷ፣ የሰላም ባለቤት የሆነውን እግዚአብሔር የማያስደስት፣ ያላትን ክብርና ዝና ዝቅ የሚያደርገው ስለሆነ፤ በሀገራችን ውስጥ ሲንፀባረቅ ለቆየው የመለያየት መንፈስ፣ እኛም በየፊናችን አስተዋጽኦ አላደረግንም ወይ? ብሎ ራስ ራስን መጠየቅ፡፡
3. ዕርቀ ሰላሙ፣ በውጭ ሀገርና በሀገር ውስጥ ባለው ሕዝበ ክርስቲያን በጉጉት የሚጠበቅ ቢሆንም፤ ከዚህ በፊትም ከ2 ጊዜ በላይ የተደረጉ ጥረቶች ውጤታቸው እና ችግራቸው ምን እንደሆነ ሳይታወቅ እንዲሁ የቀረ ነው፤ በመሆኑም በፊታችን ሐምሌ 2010 ዓ.ም ባለው ድርድር፣ ዕርቀ ሰላም ላይ፣ መድረስ አለመቻል ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ዕርቅና ሰላም የከፈለልንን ዋጋ እንደቀላል ማየት ነው ብሎ በማመን፣ ዕርቀ ሰላሙ ሳይቋጭ ከተያዘው የድርድር ጊዜ (ሐምሌ 2010 ዓ.ም) ማለፍ የለበትም ብሎ መነሣት፡፡
4. ዕርቀ ሰላሙ፡- ሙሉ ለሙሉ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ በመሆኑ፣ ከቅድስት ቤተክርስቲያን ጥቅም አንፃር የሚታይና የሚመዘን እንጂ፣ በጉዳዩ ዙሪያ ካሉ፣ የግል ፍላጐቶች፣ አመለካከቶችና አቋሞች አንፃር እንዲመራ የሚተው አለመሆኑን ማመንና መቀበል፡፡ “ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር” እንዲል በዚህ ወቅት ሁሉም ሰው ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ መነሣቱ እውነትም የይቅርታና የሰላም መምጫ ጊዜው ደርሶ ነው ብሎ በቅንነት መነሣት ይገባል፡፡
5. በአባቶች መካከል ለድርድር የሚቀርቡ ሐሳቦች እና ድርድሩ የሚመራበት መንገድና ስልት፣ ለቅድስት ቤተክርስቲያን ጠቃሚ የሆነ ነገር ማስገኘት የሚችል መሆኑን ማረጋገጥ ስለሚገባ፤ የተሻለውን እየተስማሙ መምረጥና መያዝ፣ ጥሩ መነሻ የሌለውን ሐሳብ ከዚህ ወገን ከዚያ ወገን የመጣ ነው ሳይባል፣ ከላይ በተራ ቁጥር 4 ከተገለጸው አኳያ ገንቢ የሆኑ ሐሳቦችና አቅጣጫዎች እየቀረቡበት፣ ግትር ሳይሆኑ፣ በሁሉም የባለቤትነት ስሜት እንዲዳብር፣ ነፃ ሆኖ መቀበልና ማንሸራሸር፡፡
6. በሁለቱም ወገን ተደራዳሪ የሚሆኑ አባቶች፣ በድርድሩ ላይ የሚነሱ ሐሳቦችና የማስማሚያ ነጥቦች ቅቡልነት ያላቸው መሆኑን በማረጋገጥ ይሁንታ የሚሰጡት፤ ከላይ በተራ ቁጥር 4 ላይ ከተገለጸው ዓላማ አንጻር እንጂ፣ ሲንፀባረቅ ከቆየና ቀደም ብሎ ከተያዘ አቋም አኳያ ጽንፍ በመያዝ እንዳይሆን ራስን መፈተሽ፡፡
7. ውጭ ሀገርም ሆነ ሀገር ውስጥ ያለው ሕዝበ ክርስቲያን ዕርቀ ሰላሙን በጉጉት የሚጠብቀው ስለሆነ፤ መስማማት ያልተቻለባቸውን ነጥቦች አደራዳሪዎች ለይተውና ቀርፀው በማቅረብ ላለመስማማት የተያዙትን አቋሞች ያንፀባረቋቸው ወገኖች፣ የገለጿቸውና የእነሱ መሆናቸውን በቅድሚያ እንዲያረጋግጡ በማድረግ፣ እነዚህን ነገሮች (ልዩነቶች) በሚዲያ ምእመኑ እንዲያውቃቸው በማድረግ ምእመናን ልዩነቱ እንዲፈታ የድርሻቸውን እንዲወጡ ማድረግ፡፡
8. ስምምነት ሂደት በመሆኑ፤ ድርድርና ብዙ ጊዜ በማይወስዱ ዋና ዋና በሆኑ ጉዳዮች ላይ ዕርቀ ሰላም ለመፍጠር የሚያስችሉ ግንባር ቀደም የሆኑ ነጥቦችን ለይቶ መስማማት፡፡ ከዚህ በመቀጠልም በአደራዳሪዎች አማካኝነት በቀጣይ ሊታዩ የሚገባቸውን ርእሰ ጉዳዮች ዝርዝርና የሚታዩበትን ሁኔታ አቅጣጫ ማስቀመጥ፡፡
9. በማንኛውም ደረጃ የሚገኙ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አባቶችና ምእመናን፤ ለዕርቀ ሰላሙ መሳካት እግዚአብሔርን በጸሎት እየጠየቁ፣ አስፈላጊውን ዕገዛና ድጋፍ ማድረግ፡፡ አደራዳሪዎችና ሚዲያዎችም ለሕዝበ ክርስቲያኑ መድረስና መታወቅ ያለበትን መረጃ አስፈላጊነቱን በማየት ሳይዛባ በወቅቱ ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ፡፡ አጋዥና ወሳኝነት ያለው ስለሆነ«አባቶች ዕርቀ ሰላምን በመፍጠር፤ ለቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎትና ለሀገራዊ መግባባት ወሳኝ ሚና ሊጫወቱ ይገባል!» በማለት ማኅበሩ መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ምንጭ፤ሐመር  መጽሔት 26ኛ ዓመት ቁጥር 2 ሰኔ 2010 ዓ.ም

  Ethiopia is our great home built by the bones of our ancestors!!! According to our fathers, our mother, our wife, our sister ……..it is al...